የባሕርዳር ከተማ ምክር ቤት የግል የመኖሪያ ቤት ኪራይ ላልተወሰነ ጊዜ ጭማሪ እንዳይደረግ አዲስ ጊዜያዊ ደንብ መርምሮ አጸደቀ።

90

ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ ምክር ቤቱ ባካሄደው 4ኛ ዙር ምርጫ 11ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 26ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ያልተገባ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ጭማሪ ላልተወሰነ ጊዜ መገደብን በተመለከተ በሚመለከተው አካል ተዘጋጅቶ የቀረበለትን ረቂቅ ደንብ ቁጥር 20/2016 በቋሚ ኮሚቴ እና በፍትሕ አካላት ከመረመረ በኋላ ደንቡ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዲኾን ወስኗል።

ይህም በአዋጅ ቁጥር 245/2009 አንቀጽ 2 በተቀመጠው ድንጋጌ መሰረት የኢትዮጵያዊነት የቀደመ የመተሳሰብ እና የመረዳዳት እሴትን ባልጠበቀ መንገድ የኑሮ ውድነት መባባስን ተከትሎ የግል መኖሪያ ቤት ኪራይ ጭማሪ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ በመምጣቱ ማረጋጋት ያስችል ዘንድ ተግባራዊ እንዲኾን ተወስኗል።

ለከተማዋ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ትልቅ ተግዳሮት የኾነውን የቤት ኪራይ ጭማሪ ፦

👉መንግሥት በጥናት የተደገፈ አሠራር አውጥቶ ቋሚ በኾነ ሕግ እና ደንብ እንዲመራ በማድረግ ችግሩን እስኪፈታ
👉የአከራይ እና ተከራይ መብት እና ግዴታ ግልጽ አሠራር እስኪቀመጥለት
👉 በአሁኑ ወቅት የአከራይ እና ተከራይ መልካም ግንኙነት እንዳይሻክር
👉 ለተባባሰ ትርምስ እንዳይዳረግ በባሕርዳር ከተማ ሁሉም ቀበሌዎች የሚገኙ አከራዮች ላልተወሰነ ጊዜ ምንም ዓይነት ጭማሪ ማድረግ እንደማይቻሉ በምክርቤቱ ተወስኗል።
በዚህም መሠረት:-
👉ማንኛውም የባሕርዳር ከተማ የመኖሪያ ቤት አከራይ የሚያከራየውን ቤት ወይም ዶርም ብዛት ለክፍለ ከተማ ወይም ቀበሌ አሥተዳደር ማሳወቅ አለበት፣
👉ማንኛውም አከራይ ይህ ደንብ እስካልተሻሻለ ድረስ በዚህ ወቅት መጨመርም ኾነ ተከራይን ማስለቀቅ አይችልም፣
👉ቤቱ እድሳት የሚያስፈልገው እንደኾነ ከታመነበት እንኳ በሁለቱም ወገን ስምምነት ተደርጎ ሥራው ሲጠናቀቅ ተከራዩ ተመልሶ እንዲገባበት መደረግ አለበት፣
👉አከራዩ ከተከራይ ጋር የተስማማበት የኪራይ ዋጋ የሚገልጽ ውል፣ የተከራይ ማንነት፣ አድራሻ እና የሥራ ሁኔታ የመያዝ ግዴታ አለበት፣
👉በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 6/2015 ውስጥ ታስቦ የተደረገ የቤት ኪራይ ጭማሪ ወደ ነበረበት የኪራይ ዋጋ መመለስ አለበት፣
👉ማንኛውም ተከራይ የተከራየበትን ቤት ደኅንነት፣ ንጽሕና እና መሰል ጉዳዮችን የመጠበቅ፣ ኪራይ በወቅቱ የመክፈል፣ ሕገ ወጥ ተግባር ያለመፈጸም ግዴታ እንዳለበት የሚሉ እና መሰል ውሳኔዎችን አስተላልፏል።
ይህንን የሚተላለፍ አካል ቢኖር በአንቀጽ 10 ደንብ እንደተጠቀሰው የቤት ኪራይ ዋጋ የሚጨምር ሲኖር ለአካባቢው ፖሊስ ጥቆማ በመስጠት በሕግ እንዲጠየቅ ከማድረግም በላይ በነጠላ ቤት ወይም በአንድ ክፍል ጭማሪ ያደረገ 10 ሺህ፣ በሙሉ ግቢ ላይ ጭማሪ ያደረገ ደግሞ የ25 ሺህ ብር ቅጣት በመወሰኑ በገቢዎች በኩል በደረሰኝ እንዲከፍል የሚደረግ መኾኑ ተገልጿል። መረጃው የባሕርዳር ከተማ ኮሙኒኬሽን ነው።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአሜሪካ የዓለም የክለቦች ዋንጫ ሊደረግ ነው፡፡
Next article“ለሰላም እና እርቅ የሚደረጉ ጥረቶች ስኬታማ የሚኾኑት በመተማመን፣ በመተባበር እና በመነጋገር ነው” ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ