በአሜሪካ የዓለም የክለቦች ዋንጫ ሊደረግ ነው፡፡

49

ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አሜሪካ እ.ኤ.አ በ2025 በአዲስ መልኩ የተቋቋመውን የዓለም የክለቦች ዋንጫ ታስተናግዳለች ሲል አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል።

የዓለም እግር ኳስ የበላይ አሥተዳዳሪ አካል (ፊፋ) በአዲስ ባሻሻለው ሕግ መሰረት (Mundial de Clubes FIFA) በሚል መጠሪያ 32 ቡድኖችን የሚያሳትፍ የዓለም የክለቦች ዋንጫ በ2025 በአሜሪካ እንደሚካሄድ ከሰሞኑ አስታውቋል፡፡ ውድድሩ በአራት ዓመት አንድ ጊዜ እንደሚከናወንም ነው ፊፋ የጠቆመው፡፡

የፊፋ የላይኛው ምክር ቤት እ.ኤ.አ ከሰኔ 15 እስከ ሐምሌ 13/2025 ለሚካሄደው የዓለም የክለቦች ዋንጫ ከወዲሁ መርሆዎችን አዘጋጅቶ ማጽደቁን ከሰሞኑ በጅዳ ሳዑዲ አረቢያ ካደረገው ውይይት በኋላ አስታውቋል፡፡

ከመርሆዎች አንዱ ውድድሩ በአራት ዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ይካሄዳል የሚለው ይገኝበታል፡፡ የፊፋ ፕሬዚዳንት የጂያኒ ኢንፋንቲኖ እንዳሉት በውድድሩ የየኮንፌዴሬሽን የክለቦች ሻምፒዮናዎችን በቀጥታ ያሳትፋል ሲሉ ተናግረዋል።

በውድድሩ አውሮፓ 12 ቡድኖችን ያሳትፋል ተብሏል፡፡ ስድስት ቡድኖች ደግሞ ደቡብ አሜሪካን የሚወክሉ ይኾናሉ፡፡ ከእስያ፣ አፍሪካ፣ ሰሜን እና መካከለኛው አሜሪካ አራት ቡድኖችን ተሳታፊ ደርጋሉ፡፡ ከኦሺኒያ እና ከአስተናጋጇ ሀገር አሜሪካ ሁለት ቡድኖች የሚሳተፉ ይኾናል ሲል ቢቢሲ ስፖርት በድረ ገጹ አስነብቧል፡፡

በስምንት የምድብ ድልድል አራት ቡድኖች ይሳተፉበታል፡፡ ከየምድቡ የተሻለ ነጥብ የሚኖራቸው 16 ቡድኖች ደግሞ ወደ ቀጣዩ ዙር አላፊ ያደርጋቸዋል፡፡

የዓለም የእግር ኳስ ተጫዋቾች ማኅበር “በፊፋ እቅድ ደስተኛ አይደለሁም” በማለት ተቃውሞውን አሰምቷል። ፊፋ ያሳለፈው ውሳኔ የተጫዋቾችን የሥራ ጫና እንዲሁም አእምሯዊ እና አካላዊ ጤንነትን ግምት ውስጥ ያስገባ አይደለም ሲል መሞገቱን አሶሸትድ ፕሬስ በዘገባው ጨምሮ ጠቁሟል፡፡

በተያያዘ ዜና ቺሊ የ2025 የፊፋን ከ20 ዓመት በታች እንዲሁም ፖላንድ የ2026ን የፊፋ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች የዓለም ዋንጫ እንደሚያዘጋጁ ታውቋል።

በሙሉጌታ ሙጨ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ጅሮና” የላሊጋው ክስተት
Next articleየባሕርዳር ከተማ ምክር ቤት የግል የመኖሪያ ቤት ኪራይ ላልተወሰነ ጊዜ ጭማሪ እንዳይደረግ አዲስ ጊዜያዊ ደንብ መርምሮ አጸደቀ።