“ጅሮና” የላሊጋው ክስተት

34

ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የስፔን ላሊጋ የሪያል ማድሪድ እና ባርሴሎና የበላይነት መለያው ነው። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከሁለቱ ያመለጠው ስኬትም የዲያጎ ሴሞኒው አትሌቲኮ ማድሪድ ድል ነው።

በዘንድሮው የውድድር ዓመት ግን አዲስ ነገር የሚታይ ይመስላል። “ጅሮና” የላሊጋው ክስተት ኾኖ ብቅ ብሏል። ከአራት የውድድር ጊዜያት በፊት ከላሊጋው ወርዶ የተመለሰው “ጅሮና” ድንቅ እንቅስቃሴን እያደረገ ነው። በላሊጋው 16 ጨዋታዎች አድርጎ 13ቱን አሸንፏል። ሁለቱን አቻ ተለያይቷል። ብቸኛ ሽንፈቱ በሪያል ማድሪድ ነው የገጠመው ።

በስፔናዊ አንጀል ሚቸል የሚሰለጥነው “ጅሮና” ባለፈው ሳምንት ባርሴሎናን ካሸነፈ በኋላ ስለጥንካሬው ብዙ እየተባለለት ነው።በሜዳው የ4ለ2 ሽንፈት ያስተናገደው የባርሴሎናው አሠልጣኝ ዣቪ ከጨዋታው በኋላ “ለጅሮና ክብር መስጠት አለብን” ሲል ተናግሯል።

ቶክ ስፖርት የተሰኘው የመረጃ ምንጭ ጅሮናን “አዲሱ ሌስተር” በሚል ገልጾታል። ሌስተር በአውሮፓዊያኑ ዘመን አቆጣጠር ሳይጠበቅ የፕሪሜር ሊጉን ዋንጫ ማንሳቱን በማስታወስ።

በተለየ የቡድን አንድነት ሳቢ እግር ኳስን እያሳየ ያለውን ጅሮና ይህን ገድል የመድገም ብቃት እያሳየ መኾኑን አትቷል።ከጥንካሬው በተጨማሪ የባርሴሎና መድከምም እንደ ጥሩ እድል ተቆጥሮለታል።

ጅሮና በ17ኛ ሳምንት ከአልቬስ ጋር የሚያደርገውን ጨዋታ ውጤት ሳይጨምር በላሊጋው 41 ነጥብ ሠብሥቧል። ይሄ ውጤቱም ከባርሴሎና በስድስት፣ ከአትሌቲኮ ማድሪድ ደግሞ በሰባት ነጥብ በልጦ እንዲገኝ አድርጎታል። ቀሪ ጨዋታውን ካሸነፈም ሪያል ማድሪድን በሁለት ነጥብ በልጦ ላሊጋውን ይመራል።

የውድድር ዓመቱ ሲጀመር ግባችን በላሊጋው መቆየት ነው ያሉት የቡድኑ አሠልጣኝ ሚቸል አሁን ለላሊጋው ዋንጫ ዋነኛ ተፎካካሪ ቡድንን እየመሩ ነው ተብለው እየተሞገሱ ነው።

የቡድናቸው የስኬት ልክ በውድድር ዓመቱ መጨረሻ የሚታይ ቢኾንም ለጊዜው የላሊጋው ” ክስተት” የኾነው ቡድናቸው የላሊጋው ድምቅት ኾኖ የብዙዎችን ትኩረት ስቧል።

በአስማማው አማረ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ድርድሩ በህዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌትና አለቃቀቅ ደንቦችና መመሪያዎች ላይ ስምምነት ለመድረስ ያለመ ነው” አምባሳደር ስለሺ በቀለ (ዶ.ር)
Next articleበአሜሪካ የዓለም የክለቦች ዋንጫ ሊደረግ ነው፡፡