
ባሕር ዳር: ታኅሳስ 8/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ባለፉት አምስት ወራት ከ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በወባ በሽታ መያዛቸውን የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ በጤና ሚኒስቴር የበሽታዎች መከላከል እና መቆጣጠር የወባ እና ሌሎች ትንኝ ወለድ በሽታዎች መከላከል እና መቆጣጠር ዴስክ ኀላፊ ጉዲሳ አሰፋ ባለፉት አምስት ወራት ከ4 ሚሊዮን 587 ሺህ 490 በላይ ሰዎች ምርመራ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት፡፡
ከነዚህም ውስጥ 1 ሚሊዮን 575 ሺህ 442 የወባ ሕሙማን ኾነው በመገኘታቸው አስፈላጊውን ህክምና እንዳገኙ ገልጸዋል፡፡ አቶ ጉዲሳ እየጨመረ የመጣውን የወባ ወረርሽኝ ለመከላከል በሁለት ዓመት ውስጥ ከ20 ሚሊዮን በላይ አጎበር መሠራጨቱን ገልጸዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ ከ330 ሺህ በላይ አጎበሮችን ለክልሎች ከማሠራጨት በተጨማሪ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ቤቶች የወባ ትንኝ መከላከያ ኬሚካል መረጨታቸውንም ገልጸዋል፡፡ከስድስት ሺህ በላይ ባለ 5 ሊትር ፀረ-እጭ ኬሚካል ወደ ሁሉም ክልሎች ተሠራጭቶ ቋሚ የወባ መራቢያ ቦታዎች በሚገኙባቸው አካባቢዎች ርጭት መካሄዱንም አስረድተዋል፡፡
ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ባለፉት ሦስት ተከታታይ ዓመታት በሽታው ባልተጠበቀ መልኩ እየጨመረ መሄዱን የገለጹት አቶ ጉዲሳ 75 በመቶ የሚኾነው የሀገሪቱ አካባቢዎች ለወባ በሽታ ሥርጭት አመቺ በመኾኑ 69 በመቶ የሚኾነው ሕዝብ ለበሽታው ተጋላጭ ነው ብለዋል፡፡
በተለይም የአማራ እና የኦሮሚያ ክልሎች ትልቁን ድርሻ የሚይዙ ቢኾንም በደቡብ ምዕራብ ክልል፣ በደቡብ ክልል እንዲሁም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በስፋት የሚስተዋል መኾኑን አስታውቀዋል፡፡
በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የዝናብ መቆራረጥ፣ የወንዞች መድረቅ፣ የድርቅ እና ጎርፍ መከሰት፣ በየአካባቢው ያቆረ ውሃ መኖር፣ የፀጥታ ችግር ጋር ተያይዞ አገልግሎቶችን ለመስጠት አስቸጋሪ መኾን ለበሽታው መጨመር በዋነኝነት ይጠቀሳሉ ብለዋል፡፡
የወባ በሽታን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ጨምሮ የወባ መመርመሪያ እና የፀረ-ወባ መድኃኒቶችን በሁሉም ጤና ተቋማት በበቂ መጠን እና ዓይነት እንዲኖር የማድረግ፣ ያልተሰራጩ አጎበሮችን የማድረስ፣ የወባ አስተላላፊ ትንኝ እንዳትራባ ውኃ ያቆሩ ቦታዎችን የማፋሰስ እና የመደልደል ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የወባ መከላከል እና ቁጥጥር ስልቶችን በተጠናከረ መንገድ ለመሥራት እና ወደ ነበረበት ለመመለስ አዲስ ስትራቴጂ አዘጋጅቶ በመተግበር ላይ እንደሚገኝ ኢፕድ በዘገባው አስነብቧል፡፡
በዚህም የወባ በሽታ መከላከል፣ መቆጣጠር እና የማጥፋት ስልቶችን በሁሉም ደረጃ በኀላፊነት እና በተጠያቂነት እንዲሠሩ የክትትል እና የግምገማ ሥራዎች ይሠራሉ ብለዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!