
ባሕር ዳር: ታኅሳስ 8/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል በሩሲያ የማዕድን ሃብት ኤጀንሲ ኀላፊ ኢቭጌኒ ፔትሮቭ ከተመራው ልዑክ ጋር ተወያይተዋል።ለሩሲያ ባለሃብቶች ልዑክ በኢትዮጵያ ስላለው የኢንቨስትመንት አማራጮች ገለፃ ተደርጓል። በ10 ዓመቱ የልማት እቅድ እና በሀገር በቀል ምጣኔ ሃብታዊ ማሻሻያው ትኩረት ከተደረገባቸው ዘርፎች መካከል አምራች ኢንዱስትሪው አንዱ መኾኑን አቶ መላኩ አለበል ተናግረዋል።
ሀገሪቱ ለኢንዱስትሪ ምቹ ሥነ-ምህዳር እንዲሁም በቂ የሰው ኃይል እና ጥሬ እቃ እምቅ አቅም እንዳላት ጠቅሰዋል።የኢትዮ-ሩሲያ ግንኙነት ከ125 ዓመታት በላይ ማስቆጠሩን የገለጹት ሚኒስትሩ ይህን ግንኙነት በንግድ እና ኢንቨስትመንት ዘርፍ የበለጠ ማጠናከር ይገባል ብለዋል።
ሩሲያ በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በትምህርት፣ በማዕድን እና ኢነርጂ ያላትን የካበተ ልምድ ለኢትዮጵያ እንድታጋራም ጠይቀዋል።የሩሲያ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ምቹ የአምራች ኢንዱስትሪ ምህዳር መኖሩን እንዲገነዘቡ እና መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈስሱ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ከመገንባት ጀምሮ በዘርፉ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች የተለያዩ ማበረታቻዎችን እያደረገች መኾኗንም ጠቅሰዋል።ለአብነትም በዘርፉ የሚሰማሩ ባለሃብቶች የተለያዩ ማሽነሪዎችን ከቀረጥ ነፃ እንዲያስገቡ፣ የታክስ እፎይታ መስጠት፣ የፋይናንስ አቅርቦት እና የመሳሰሉትን አንስተዋል።
የሩሲያ የማዕድን ሃብት ኤጀንሲ ኀላፊ ኢቭጌኒ ፔትሮቭ በበኩላቸው ሩሲያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የረጅም ጊዜ ወዳጅነት የበለጠ ማጠናከር ትፈልጋለች ብለዋል።
የሩሲያ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮችን በመጠቀም በተለይም በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በግብርና እና በማምረቻ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ቢሰማሩ ውጤታማ እንደሚኾኑ ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ያላትን የማዕድን እና ኢነርጂ ሃብት ለዘላቂ ልማት እንድታውል የሥነ ምድር አሰሳ የጥናት አቅሟን እንድታሳድግ ሩሲያ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ ትቀጥላለች ነው ያሉት።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!