የኅብረት ሥራ ማኅበራት ለሀገር ኢኮኖሚ ያላቸውን አበርክቶ ለማሳደግ የሪፎርም ንቅናቄ መድረክ እየተካሄደ ነው።

69

አዲስ አበባ: ታኅሳሥ 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ከኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አመራሮች፣ ከከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች እና ከኮሚሽኑ ከፍተኛ አመራሮች ጋር የኅብረት ሥራ ማኅበራትን የልማት እና የዕድገት የሪፎርም ንቅናቄ መድረክ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው።

የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌታቸው መለሰ (ዶ.ር) በመድረኩ ተገኝተው የኅብረት ሥራ ማኅበራት መኖር የአባላት የተበታተነ አቅም እንዲቀናጅ፣ ፍትሐዊ የገበያ ዋጋ እንዲኖር፣ ምርት በጥራት እና በወቅቱ እንዲቀርብ፣ የሥራ ዕድል እንዲፈጠር፣ የማምረቻ ወጪ እንዲቀንስ ማኅበራዊ ፍትሕ እና እኩልነት እንዲሰፍን ማስቻላቸውን ተናግረዋል።

ኅብረት ሥራ ማኅበራት በግብርና ግብዓት አገልግሎት፣ በምርት ገበያ፣ በእሴት ጭመራ እና በመሰረተ ልማት አቅርቦት በጥራትና በስፋት እንዲያቀርቡ እንደሚሠራም አስገንዝበዋል፡፡

ዶክተር ጌታቸው ኅብረት ሥራ ማኅበራት ምርትን በአመቺና ቀልጣፋ መንገድ እንዲያስተዋውቁ፣ የሽያጭና ድህረ ሽያጭ አገልግሎት እንዲዘረጉ ለማስቻል በትኩረት ይሠራልም ነው ያሉት፡፡

የቁጠባ እና ብድር ኅብረት ሥራ ማኅበራት በራሳቸው አቅም እና ከአባላት ውጪ የአክሲዮን ፕሮጀክት ካፒታል እንዲያሰባስቡ እና የኅብረት ሥራ ባንክ እንዲያቋቁሙ ይደረጋልም ብለዋል።

በመድረኩ በክብር እንግድነት የተገኙት የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባዔ ሎሚ በዶ በበኩላቸው የሪፎርም ንቅናቄው የኅብረት ሥራ ማኅበራት የካፒታል አቅማቸውን ለማጠናከር፣ የግብርና ግብዓት እና ቴክኖሎጂ አቅራቦት ተሳትፏቸውን ለማሳደግ እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡

ምክትል አፈ ጉባዔ ሎሚ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ገበያ ድርሻቸውን ለማሻሻል እና እሴት በሚጨምሩ አግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንደስትሪዎች ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ እንደሚያስችላቸውም አስገንዝበዋል፡፡

ምክር ቤቱ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ላይ ተገቢውን ክትትል፣ ድጋፍ እና ቁጥጥር እንደሚያደርግም ገልጸዋል።አሁን ላይ የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ከ110 ሺህ በላይ መሰረታዊ የኅብረት ሥራ ማኅበራት፣ 28 ሚሊዮን በላይ አባላት፣ 403 ዩኒየን እና 5 ፌዴሬሽንን አቅፎ እየተንቀሳቀሰ መኾኑም ተገልጿል፡፡

ዘጋቢ፡- ቤቴል መኮንን

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በጦርነቱ በደረሰብኝ ጉዳት ማኅበራዊ ጫና ደርሶብኛል፤ ትምህርቴንም መቀጠል አልቻልኩም” ተማሪ ሳሙኤል መላኩ
Next articleየሩሲያ ባለሃብቶች በአምራች ኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት ዘርፍ እንዲሳተፉ ተጠየቀ።