“በጦርነቱ በደረሰብኝ ጉዳት ማኅበራዊ ጫና ደርሶብኛል፤ ትምህርቴንም መቀጠል አልቻልኩም” ተማሪ ሳሙኤል መላኩ

46

ባሕር ዳር: ታኅሳስ 8/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ባለፉት ሦስት ዓመታት በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በተከሰተው ጦርነት ከፍተኛ ቁሳዊ ጉዳት መድረሱ ይታወሳል። የጦርነት ዳፋው በዜጎች ላይ የከፋ ሰብዓዊ ጉዳት አድርሷል።የጦርነት ችግር ገፈቱ ቀማሽ ከኾኑት ውስጥ የ16 ዓመቱ ታዳጊ ተማሪ ሳሙኤል መላኩ ይገኝበታል።

ታዳጊው በሰሜን ጎንደር ዞን አዳርቃይ ወረዳ ዛሪማ አካባቢ አርባ አራቱ ትምህርት ቤት የ6ኛ ክፍል ተማሪ ነበር። ታዳጊው በወቅቱ እናት እና አባቱ መለያየታቸውን ተከትሎ ከአያቶቹ ጋር ኾኖ ለመማር ተገደደ። ይሁን እንጅ በ2013 ዓ.ም በመኖሪያ አካባቢያቸው በተቀሰቀሰው ጦርነት ታዳጊው ቀኝ እጁ ላይ ጉዳት እንደደረሰበት ይናገራል። በወቅቱ በተነሳው ጦርነት ማኅበረሰቡ ራሱን ለማዳን በየአቅጣጫው በመበተኑ የተጎዳን አንስቶ ህክምና የሚያደርስ እንዳልነበርም ነው የገለጸው፡፡

በሦስተኛው ቀን ውጊያው መቆሙን ተከትሎ ሕክምና የማግኘት አጋጣሚ ቢፈጠርለትም የትራንስፖርት ችግር ሌላው ፈተና እንደነበር ያስታውሳል። ይሁን እንጅ በወቅቱ በአካባቢው በነበረው መከላከያ ሠራዊት ተሽከርካሪ ወደ ጎንደር ተወስዶ ሕክምና ማግኘቱን ነግሮናል፡፡

በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በነበረው ጦርነት ቀኝ እጁን ያጣው ተማሪ ሳሙኤል አሁን ላይም ከሕመሙ ሙሉ በሙሉ ማገገም አልቻለም፡፡ በደረሰበት ጉዳት ማኅበራዊ ግንኙነቱ ላይ ጫና እንዳደረሰበትም ነግሮናል። “በደረሰብኝ ጉዳት ማኅበራዊ ጫናው ከፍተኛ ነው፤ የሥነ ልቦና ጉዳት ስለደረሰብኝ የእጅ ስልኬን በ6 ሺህ ብር በመሸጥ ወደ በባሕር ዳር ለመጓዝ መርጫለሁ” ብሎናል።

ታዳጊው አሁን ላይ በባሕር ዳር ከተማ ኑሮን ለማሸነፍ የጫማ ማስዋብ ሥራን ምርጫው አድርጓል፡፡ እየደረሰበት ካለው ማኅበራዊ ጫና ሽሽት ወደ ባሕር ዳር ቢያቀናም “አንበሳን ፈርቼ ዛፍ ላይ ብወጣ ነብር ጠበቀኝ” እንደሚባለው በክልሉ የተከሰተው የጸጥታ ችግር ሌላ ፈተና ኾኖበታል። በሰላም እጦት ምክንያት ሥራ በመቀዛቀዙ ለዕለት ጉርስ የሚኾን ገቢ የማይገኝበት ቀን እንደሚበልጥ ነው የገለጸው፡፡

‹‹የዞኖች ጠብ ትርፉ ለሳሩ›› እንደሚባለው በግጭቱ ዝቅተኛው ማኅበረሰብ በተለይም ደግሞ አካል ጉዳተኞች ይበልጥ ተጎጅ መኾናቸውን ትዝብቱን አጋርቶናል። በችግሩ ምክንያት አሁንም የመማር ፍላጎቱን ማሳካት አለመቻሉንም ነው ያነሳው። ለሰላም ሁሉም ዘብ መቆም ግዴታ አድርጎ መሥራት እንደሚገባ ምከረ ሃሳቡን ገልጿል፡፡

ሌላኛው በጎንጅ ቆለላ ወረዳ ገረገራ ከምትባል ቦታ እንደመጣ የተናገረው እና ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገው የ17 ዓመት ታዳጊ ነው። ታዳጊው የ10ኛ ክፍል ተማሪ ሲኾን በወረዳው በተከሰተው የሰላም እጦት እስከ አሁን ትምህርት ቤቶች ዝግ መኾናቸውን ነግሮናል። አሁን ላይ በባሕር ዳር ከተማ በጫማ ማስዋብ ሥራ ላይ ተሰማርቶ ይገኛል። ሰላምን ፍለጋ ባሕር ዳር የከተመው ታዳጊ ተመሳሳይ ችግር አጋጥሞታል፡፡ አንዳንድ ጊዜ በሚከሰተው ግርግር ሥራ ሣይሠራ የሚውልበት ጊዜ እንደሚበልጥ ነው የሚያነሳው፡፡ በጫማ ማስዋብ በሚያገኛት ገቢ ቤተሰቡን እንደሚያግዝ የገለጸው ታዳጊው ካለው የኑሮ ውድነት ጋር ፈተናው “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንደኾነበት ነግሮናል።

ታዳጊዎቹ አሁን ያለውን ችግር በውይይት በመፍታት ማኅበረሰቡን ከጥፋት መታደግ እንደሚገባ ምክረ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሰላም ከሌለ ማሳው ጦም ያድራል፤ ገበያውም ይራባል”
Next articleየኅብረት ሥራ ማኅበራት ለሀገር ኢኮኖሚ ያላቸውን አበርክቶ ለማሳደግ የሪፎርም ንቅናቄ መድረክ እየተካሄደ ነው።