“ሰላም ከሌለ ማሳው ጦም ያድራል፤ ገበያውም ይራባል”

37

ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ከሰላም የበለጠ ነገር ምን ይኖራል? በሰላም ወጥቶ ከመግባት የዘለለ ትርፍ ምን ይገኛል? ሰላም የሁሉም መሠረት የሁሉም መፈጸሚያ አይደለምን?

የሀገሬው ሰው ጎህ ሲቀድ ገና ከተኛባት መደቡ ቀና ብሎ “ቸር አውለኝ፣ ሰላም አውለኝ፣ ቀኔን ባርክልኝ” ይላል። ቀኑን የሚጀምረው ስለ ሰላም ጸልዮ፣ ሰላም ያውለው ዘንድ ለአምላኩ አደራ ሰጥቶ ነው። ከዋለበት ውሎ ከቤቱ በገባ ጊዜም፣ ከድካሙም ሊያርፍ ወደ መደቡ በተመለሰ ጊዜ” ሰላም ያዋልከኝ አምላክ የተመሰገንህ ኹን፣ ሰላም እንደአዋልኸኝ ሰላም አሳድረኝ” ብሎ አደራውን ለአምላኩ ሰጥቶ ጋደም ይላል።

የንግግር መጀመሪያው፣ የንግግርም መፈጸሚያው ሰላም ነው። የሀገሬው ሰው ሰላም ካለ መደቡ አትጎረብጠውም፣ የጣመ ከመብላት፣ የጣፈጠ ከመጠጣት፣ በተመቸ ማረፊያ ከመተኛት አስቀድሞ ሰላም ይኖር ዘንድ ይመኛል።

ሰላም ከሌለ ማሳው ጦም ያድራል፣ ገበያው ይራባል፣ ወተት እና እሸት ይጠፋል። ሰላም ከሌለ ልጆች አያድጉም፣ አረጋውያን አይጦሩም፣ ልጆችን አይመርቁም፣ ታሪክ አያስተምሩምና። ሰላም ከሌለ ሕሙማን አይድኑም፣ ነብሰጡር እናቶች ከምጣቸው አይገላገሉም፣ ሰላም ሁሉንም ያሳምራል። ሰላም ሁሉንም ያስውባል። ለዛም ነው በሰላም የከፈተውን ቀኑን በሰላም ደምድሞ ጋደም የሚለው።

በዚህ ሰሞን በጠፋው ሰላም መኖርን የሚሽቱ ሞተዋል፣ ሮጠው ያልጠገቡ ቆስለዋል፣ የእለት ጉርስ የሚሹ ጉርስ አጥተዋል፣ ገበያው ተርቧል፣ እናቶች በገባው ተንከራትተው የፈለጉትን ሳይዙ ተመልሰዋል፣ ብዙ አስበው ጥቂት ብቻ ሸምተዋል። ለወትሮው በቀን በቀን ሲጨምር የነበረው ዋጋ ዛሬ ላይ ከማይቀመስበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ድንጋይን እንደመሸከም ሆኗል።

አምራች እና ሸማች እንዳይገናኝ መንገዶች ተዘጋግተዋል፤ አርሶ አደሮች ከጎተራው ዝቀው ገበያውን እንዳያጠግቡ የሰላም ጎዳና አጥተዋልና ሸምተው የሚጎርሱ፣ ልጆቻቸውን የሚያቀምሱት ተችግረዋል። ለልጆቼ ምን ላቅምስ የሚሉት በርክተዋል።

የሰላም እጦት ባስከተለው ችግር ከተፈተኑ እናቶች መካከል ከአንደኛዋ ጋር ቆይታ አድርጌያለሁ፡፡ ሰላም ሲታጣ የገጠማቸውን የሕይወት ውጣ ውረድ እና የመኖር ፈተና አጫውተውኛል። ወይዘሮ ባይብኝ አግማሴ ይባላሉ። የባሕርዳር ከተማ ነዋሪ ናቸው። የነጠላ ጫፍ ፈትለው በሚያገኟት ትንሽ ገንዘብ ኑሯቸውን ይመራሉ፣ ልጆቻቸውን ያሳድጋሉ።

እናት ባይብኝ ስለ ኑሯቸው ሲነግሩኝ “የነጠላ ጫፍ ፈትዬ ነው የምኖረው፣ ሰላም ሲጠፋ ከችግር ላይ ችግር ተደራረበብን፣ ዱባ ልገዛ ሄጄ መቶ ሃምሳ ብር ተብዬ መጣሁ። ቀደም ሲል አንድ ዱባ በብር ከሃምሳ ሣንቲም ገዝተን ልጆቻችንን እናሳድግ ነበር፡፡ አሁን መቶ ሀምሳ ብር ሲባል ምን ይባላል? ከርተት ብዬ መጣሁ። በሬ ሲበላው ይኖር የነበረ ዱባ መቶ ሃምሳ ብር! መቶ ሃምሳ ብር የት አግኝቼ? ሃብታም ዐይኑ ያየውን ገዝቶ ሲሄድ እኔ ዓይኔ ዞሮ ዞሮ ቤቴ መጥቻለሁ” ነው ያሉኝ።

እኒህ እናት ከችግር የመውጫ መንገዶቻቸውን ሁሉ የሰላም እጦት እንደዘጋጋባቸው እና ከችግር ላይ ችግር እንደደራረበባቸው ነግረውኛል። በሃሳብ ውለው በሀሳብ ያድራሉ። “ከጤፉ ገበያ ገባሁ አሥራ ሥድስት አሉኝ። ደስ ብሎኝ ልገዛ ስልስ ለካ አሥራ ስድስት ሺህ ኖሯል፣ እኔ ስላልተማርኩ ቁጥሩን አላውቀውም።

ከዳጉሳውም፣ ከበቆሎውም ገበያ ብገባ ከአቅሜ በላይ ነው፤ ስዞር ውዬ ጭንቅላቴ ዞሮ ግፊት እና ስኳር አለብኝ እሱ ጨምሮብኝ፣ በፀሐይ ስመታ ውዬ መጥቼ ከቤቴ ተኛሁ” ይላሉ የኑሮውን ፈተና ሲነግሩኝ።

ገበያ ሊገበዩ ወጥተው ሀዘን እና ጭንቀት ሸምተው ተመለሱ። የተራቆተች ማጀታቸውን ሊሞሉ ገበያ ሄደው ሃሳብ ይዘው መጡ። ሃሳብ አርግዘው እንቅልፍ የሌለው ሌሊት አሳለፉ። ይህ ዘመን ለእርሳቸው እና ለእርሳቸው ቢጤ አይኾንምና። ደሃ ገብይቶ የማይመለስበት፣ ኑሮ የማይቀመስበት ደረጃ ላይ ደርሷልና።

“ሰላም ቢኖር በዚህ ድልድዩ ተሰበረ፣ በዛ ድልድዩ ተሰበረ ባይባል፣ ሀገሬ ወይን ይበቅልባት እና ሁሉን ታመርት ነበር። እኛ ደሃዎቹ እንዴት አድርገን አንድ ኪሎ ሽንኩርት መቶ አርባ ብር ገዝተን እንበላለን?! እንዴት ይኾናል? ከገበያው ሄደህ ስትጠይቅ የለም ነው የሚሉህ። ከዚህ ሁሉ መከራ ወንድማማቾች ሰላም ቢኾኑልን እኛ ደሃ እናቶች ከጉዳት እንድናለን፡፡

አያዝኑልንም? እኛ ደሃ እናት አባቶቻቸው እኮ ነን። ሠርተን ካልበላን እንዴት ብለን እንኖራለን? አንድ ቤት ውስጥ እኮ ሰባት ስምንት ልጅ ያለው ሰው አለ። እናት እና አባቱን የሚጦር አለ። እንዴት ነው የሚኖረው ታዲያ? ገበያ ሲቆም ማነው የሚሞተው? እኛ ደሃዎች አይደለንም? ደሃዎች ነው ቀድመን የምንሞተው፣ ከየት አምጥተን እንበላለን? መንገድ ከተዘጋ፣ በየሀገሩ ያለው ምርት ካልተዘዋወረ እንዴት ብለን እንኖራለን? አሁን እኮ እርስ በእርሳችን በጥላቻ እየተያየነ ነው” ነው ያሉኝ እናት ባይብኝ የኑሮን ክብደት እና ቀጣይ እጣ ፋንታ ሲነግሩኝ።

መንገዶች ሲዘጋጋጉ ችግሩ በዝቶባቸዋልና። ወንድሞቻችን፣ ልጆቻችን ለምን ይጋደላሉ? ስለ ምን አባትና ልጅ ይገዳደላሉ? ይላሉ አሁን ያለውን ግጭት ሲገልጹ። እንኳን ሠርቶ ለመብላት ወጥቶ ለመግባት ተቸግረናል፣ የሚያስፈራን ብዙ ነው ይላሉ።

“ተስማምተው ሀገር ሰላም ያድርጉልን፣ እኛም ሕመምተኞቹ እንኑር፣ የአንዱን መድኃኒት ስንወስድ የሌላው ይታጣል፣ ሀገር ሰላም ካልኾነ የት ነው የምንሄደው? ልጆቻችን ማታ ምጥ ቢያዙ እንዴት አድርገን ነው ሀኪም ቤት የምንወስዳቸው? ወላድ ተጨንቃ እኮ ነው ያለች። መኾን የሌለበት እኮ ነው የኾነው። ለማን አቤት እንበል? ጭንቀታችንን ለማን እንናገር? ተው ስሙን” ነው ያሉኝ ችግራቸውን እና ምሬታቸውን ሲነግሩኝ።

እኒህ እናት ችግሩ እንደበረታባቸው፣ ሃሳብም እንደበዛባቸው፣ የልጆቻቸው ነገር አላስተኛ እንዳላቸውም ነግረውኛል። “ልብስ ለብሶ የሚሄደው ሁሉ ጤነኛ እና ደስተኛ እንዳይመስልህ፣ ማሽላውን ነቀዝ እንደሚበላው ሁሉ ውስጡ ነቅዟል። ምን ይመጣብኝ እያለ። አንድ ጥይት ሲተኮስ ወዮ ልጆቻችንን የት እንክተታቸው እያልን እንጨነቃለን። አይ ወላድ መከረኛዋ እንደ እንጨት ቆማ ነው የምታመሸው። ሀገር ሰላም ቢኾን እንደዚህ እንጨነቃለን? አንጨነቅም። ሕመሙንም ቢኾን እንችለው ነበር” ነው ያሉት።

እናት ባይብኝ በእናት አንጀታቸው፣ ሳግ እየተናነቃቸው ልጆቻቸው ለሚኾኑ ሁሉ የተማጽኖ ቃል አቅርበዋል” ለእኛ ለደሃ እናቶቻቸው ሲሉ ሰላም ያውርዱ። ሃብታምስ በገንዘቡ ይበላል። እኛ የት እንገባለን። እኛ ከምኑ እንግባ፣ ማታ ሲመጣ ጣና ነው ወይስ ዓባይ ነው መግቢያችን” ብለዋል። ደሃዎች እንዳይራቡ፣ እጅ ያጠራቸው እንዳይጠሙ ሰላም ይኖር ዘንድ ግድ ነውና።

መቼም በዚህ ሰሞን የማይሰማ የለም፣ የማይባል የለም። ወደደሳሳ ጎጇችን የዘለቅህ እንደኾነ እንባን የሚያስፈስስ፣ አንጀትን የሚያላውስ የሕይወት ፈተና ሞልቷል። ሰላም ለያዛት ቀላል ትመስላለች። ያጣት እና የተቀጣባት ግን ያውቃታል።

“ሌላውስ ገዝቶ ይበላል፣ እኛ የት ሄደን እንብላ? መድኃኒት በምን እንግዛ? እንዴት ኾነን እንኑር? እንዴትስ ኾነን ይሄን ጊዜ እንለፈው? ደረቆት ቆልታ የምታሳደግ እናት ልጆቿን ታጣለች፣ ሰላም ካለ ርሃቡን እንችለዋለን፣ ርሃብ እና ሰላም ማጣት ግን አይኾንም” ነው የሚሉት።

እሳቸው ብቻ አይደሉም የተቸገሩት። እንደ እርሳቸው ሁሉ እልፍ አዕላፍ እናቶች ተቸግረዋል። ደሳሳ ጎጇቸውን ዘግተው አንብተዋል። ነገ ለልጆቻችን ምን እንስጥ እያሉ ተጨንቀዋል። እየተጨነቁም ነው።

“ለአንደኛው ቆርሰን ለሌላኛው ምንሰጠው የለንም፡፡ ገበያ ሂዱ እስኪ ደሃ ገብይቶ አይመጣም እኮ፣ እኛ የት እንድረስ፣ ለምንድን ነው ይሄን የማታውቁልን፣ ልጆቻችን እኮ ሲወጡ እያለቀስን ነው” ነው ያሉኝ። ስንቶች የእናቶች ለቅሶ ገብቷቸው ይኾን? ስንቶችስ የእናቶች ረሃብ ርቧቸው ይኾን? ስንቶችስ የእናቶች ጥማት ተሰምቷቸው ይኾን?

“ወንድሞቼ፣ ልጆቼ ለድሃ እናቶታችሁ ስትሉ ሰላም ፍጠሩልን። ለእኛ ለድሃዎች ስትሉ ሰላምን ምረጡ። እኛ የት እንሂድ? ከምኑ እንጠጋ እያልን ነው? ገንዘብም ቢኖር ሀገር ሰላም ካልኾነ አይበላም። የአንድ ሰው ልጆች ምን መጥቶባችሁ ነው የምትገዳደሉ? ለእኛ ለእናቶች ስትሉ ሰላም ፍጠሩ እባካችኹን” ነው ያሉት የእናት አንጀታቸው እየተንሰፈሰፈ። በሀገሬ የእናት ቃል ይከበራል። የእናት ትዕዛዝ ይፈጸማል፡፡ አንድ እውነት አለ የሚያለቅሱ እናቶች በምድሯ ሞልተዋል። እናቶች ደግሞ ይስቁ ዘንድ ሰላምን ይሻሉ።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየክልሉ መንግሥት ያቀረበው የሰላም ጥሪ ከሕግ አንጻር እንደት ይታያል?
Next article“በጦርነቱ በደረሰብኝ ጉዳት ማኅበራዊ ጫና ደርሶብኛል፤ ትምህርቴንም መቀጠል አልቻልኩም” ተማሪ ሳሙኤል መላኩ