
ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የተከሰተውን የሰላም መደፍረስ ለመፍታት የክልሉ መንግሥት ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕዝ ጋር በመነጋገር ታጥቀው ለሚንቀሳቀሱ አካላት ለሰባት ቀናት የሚቆይ የሰላም ጥሪ አቅርቧል።
ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉት የሕግ ባለሙያዎች ዶክተር የኔነህ ስመኝ እና አቶ ፈንታሁን አምባየ በሰላም ጥሪውና ጠቀሜታዎቹ እንዲኹም በሕጋዊ ተቀባይነቱ ላይ አስተያየት ሰጥተዋል።
በሰላም ጥሪው ሂደት ታጣቂ ኃይሎች ተሳታፊ ከኾኑ ከምንም በላይ ለክልሉ ሕዝብ ጠቀሜታው የጎላ እንደሚኾን ነው ዶክተር የኔነህ የጠቀሱት። “የሰላም ጥሪው ከተጨማሪ ደም መፋሰስ፣ የሕይወት መጥፋትና ማኅበራዊ ሕይወት መቃወስ ያድናል፤ ለሰላማዊ የፖለቲካ ትግልም ዕድሉን ያመቻቻል” ነው ያሉት።
በዚህም የሰላም እጦት፣ የኑሮ ውድነት እና የማኅበራዊ መስተጋብር ችግሮች ስለሚቀረፉ ሕዝቡ ተጠቃሚ እንደሚኾን አብራርተዋል ”በግጭቱ የተሳተፉ አካላትን ተጠያቂ የሚያደርጋቸው ወንጀል ቢኖርባቸው ምህረት ያገኛሉ፤ ወደቀደመ ሕይወታቸው እንዲመለሱና ከማኅበረሰቡ ጋር እንዲቀላቀሉ ይደረጋል” ያሉት ደግሞ ሌላኛው የሕግ ባለሙያ አቶ ፈንታሁን አምባየ ናቸው።
በተለያየ ምክንያት ወደትጥቅ ትግል ለገቡ የኅብረተሰብ ክፍሎችም ጥሪውን ተቀብለው ወደ ማኅበረሰቡ ከተቀላቀሉ ከሂደቱ አውድ ጋር በተያያዘ የተፈጸሙ ወንጀሎች ካሉ እና የተጀመሩ ክሶችና ክርክሮች ካሉ እንዲቋረጡ የክልሉ መንግሥት ውሳኔ ወስኗል ነው ያሉት። ይህም ”የሰላም ጥሪውን ተቀብለው የሚመለሱትን ወደሰላማዊ ሕይወት ለመመለስ ዕድል ይፈጥርላቸዋል” ብለዋል።
”በሰላም ጥሪው መሰረት ታጣቂዎች ሪፖርት ማድረግ እና ሥልጠናውን መውሰድ ከቻሉ ያላቸውን ፖለቲካዊና ሌሎች አጀንዳዎችን በሰላማዊ መንገድ እንዲያቀርቡና ሁኔታዎች እንደሚመቻቹ ያስችላል” ያሉት ደግሞ ዶክተር የኔነህ ናቸው። ዶክተር የኔነህ አክለውም የሰላም ጥሪው ሰላም እንዲሰፍንና የሕግ የበላይነት እንዲከበር ያስችላል ብለዋል።
በዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!