
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አማካሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሀገራዊ ምክክሩ እንዲሳካ ኢትዮጵያ ለጠየቀችን ጥያቄ መልስ መስጠት ያለብን ጊዜ አሁን ነው ሲሉ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አማካሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር ዳንኤል ቅጣው ገለጹ።
ፕሮፌሰር ዳንኤል የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንን ለማማከር የተሰየመውን “አማካሪ ኮሚቴ” የሥራ ተነሳሽነትና ዝግጁነትን አስመልክተው ከኢፕድ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ “ ሀገራችን ኢትዮጵያ አስተምራናለች። ያለን ሁሉ የሀገራችን ነው። ስለዚህ የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን ብለዋል።
ሁሉም የኮሚቴ አባል ለዚህ ቁርጠኛ ነው መሆኑን የጠቀሱት ፕሮፌሰር ዳንኤል፤ የኮሚቴው አባላት ጥሩ ልምድ ያላቸውና አንጋፋ ሰዎች መሆናቸውን ጠቅሰ ዋል።
ይህን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ኢትዮጵያ ለጠየቀችን ጥያቄ መልስ መስጠት ያለብን ጊዜም አሁን ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ኮሚሽኑ ሥራው ሰፊ መሆኑን በመጥቀስ፤ የኮሚሽነሮች ዋና ሥራቸው ሌሎችን ማሠራት ጭምር እንደሆነና ብቻቸውን የ120 ሚሊዮን ሕዝብ ችግር ለመፍታት እያንዳንዱን ሥራ ሠርተው ይጨርሳሉ ብሎ መገመት እንደሚያስቸግር ገልጸዋል። ስለዚህ እነርሱን መደገፍ አስፈላጊ በመሆኑ ምክረ ሃሳብ በማቅረብ እገዛ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
በሚሠሩት ሥራ ተሳታፊዎችን የመለየት ሥነ ዘዴዎችን በማሳየት፤ ሥራው እንዴት መሠራት እንዳለበትና የወደፊት ቀጣይነት ላይ ችግር ሲያጋጥም እንዴት መፈታት እንዳለበት የሚያመላክቱና ሌሎችንም ጉዳዮች በሃሳብ ደረጃ ለማማከር ኮሚቴው ዝግጁ ሆኖ እየሠራ እንዳለ አመላክተዋል።
ኮሚሽኑም ምክረ ሃሳቡን ወስዶ የራሱንም ጨምሮ የማሻሻል ሥራውን ይሠራል ነው ያሉት። የእኛ ኃላፊነት ምክረ ሃሳብ መስጠት ነው። ትልቁ ሥራ ያለው ግን ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ጋር ነው ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ አማካሪ ኮሚቴው ምክር ይሰጣል እንጂ ለኮሚሽኑ በአዋጅ የተሰጠውን ሥራ እንደማይሠራ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በ1953 ዓ.ም፣ በ1966 ዓ.ም፣ በ1983 ዓ.ም እና በ1997 ዓ.ም የነበሩትን ሀገርን ሊለውጡ የሚችሉ መልካም አጋጣሚዎች አጥታለች ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ እንደ ሀገር በ2010 ዓ.ም የመጣውን መልካም አጋጣሚ ልናጣው አይገባም ብለዋል።
“ይህንን እኛ የምንቆጥረው እንደ አጋጣሚ ብቻ ሳይሆን እንደ መልካም እድል ነው” ሲሉም ሀገራዊ ምክክሩን ገልጸውታል። ሀገራዊ ምክክሩ ውጤታማ እንዲሆን ሕዝቡ ይህንን አጋጣሚ ተጠቅሞ ወደ ልማት፣ ወደ እድገትና ስምምነት መምጣት እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
እንደ ሀገር ከዚህ ቀደም ከንጉሣዊ አገዛዝ እስከ ኮሚኒዝም የተሞከሩት ሙከራዎች ውጤት አላመጡም ያሉት ፕሮፌሰር ዳንኤል፤ ሠላም ለማምጣት በትብብር አንዱ አንዱን አክብሮ መኖርን አማራጭ የማድረግ ሙከራው እንዲሳካ ማድረግ እንደሚገባ ጠቅሰዋል።
አማካሪ ኮሚቴው ከዚህ አኳያ ቁርጠኛ ሆኖ እንደሚሠራም ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ሕዝብም ይሄ አጋጣሚ እንዳያልፈው በቁርጠኛነት እና በልበ ሰፊነት መሥራት አለበት በማለት አሳስበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!