በአማራ ክልል የገጠመውን ችግር ሙሉ በሙሉ በመቀልበስ የሕዝቡን ሰላም ለማረጋገጥ “የጣና ቃል ኪዳን ሰነድ” ስምምነት ተፈረመ።

104

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የ2016 ዓ.ም የአምስት ወራት የሥራ እንቅስቃሴውን እና የወደፊት የሥራ አቅጣጫውን የክልል፣ የዞን እና የከተማ አሥተዳደር አመራሮች በተገኙበት በባሕር ዳር ከተማ ገምግሟል። በመድረኩ ማጠናቀቂያ ክልሉ የገጠመውን ችግር በዘላቂነት በመቀልበስ ሰላምን ለማስፈን እና የሕዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ “የጣና ቃል ኪዳን ሰነድ” ስምምነት ተፈርሟል።

ይህ ሰነድ “የጣና ቃል ኪዳን ሰነድ” የሚል ስያሜ የተሰጠው የውሳኔ ሀሳብ ሲኾን ዋና ዋና የስምምነት ነጥቦችን ያካተተ ነው።

እነሱም:-

👉በክልሉ ላይ የተጠነሰሰውን ቀውስ በመቀልበስ ዘላቂ ሰላምን መገንባት።
👉ጠንካራ የሕግ ማስከበር ሥራ በመሥራት የሚፈጠሩ ችግሮችን መቅረፍ እና ሕዝብን የሰላም፣ የዴሞክራሲ እና የልማት ተጠቃሚ ማድረግ።
👉የሕዝብን ሥነ ልቦና የሚመጥን፣ እሴቱን የሚገነዘብ እና ተጠቃሚ የሚያደርግ የመንግሥት ተቋም መመስረት፣
👉የሀገሪቱን ታሪክ በጥልቀት በመገንዘብ ጠንካራ የዴሞክራሲ ባሕል መገንባት እና ብሔራዊ ትርክትን ማጽናት።
👉በውል ተለይተው ያደሩ የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎችን ከመላ ኢትዮጵያዊያን ጋር በመኾን ዘላቂ መፍትሔ መስጠት።
👉በኢትዮጵያ ልክ ለኢትዮጵያዊነት በመቆም ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን መገንባት።
👉ሁሉንም አቅሞች በመጠቀም ጠንካራ ሕዝብ እና ሀገር ለመገንባት የድርሻን ለመወጣት ተግቶ ለመሥራት ስምምነትን የሚገልጽ ነው።

የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ፣ የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን፣ የጽሕፈት ቤቱ የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ፍስሃ ደሳለኝ፣ የፖለቲካ ዘርፍ ኀላፊው ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ.ር) እና ሌሎችም ከፍተኛ የክልል፣ የዞን እና የከተማ አሥተዳደር አመራሮች በተገኙበት ነው ስምምነቱ የተፈረመው።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በአንድ ቀን ሁለት ቃል ኪዳን”
Next articleበኩር ጋዜጣ ታኅሳስ 08/2016 ዓ.ም ዕትም