“በአንድ ቀን ሁለት ቃል ኪዳን”

108

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አንዳንድ  ቀናት አሉ ከቀናት ሁሉ የተለዩ፣ ከቀናት ሁሉ ከፍ ያሉ፣ ተለይተው የሚታወሱ፣ በታሪክ መዝገብ ላይ የማይረሱ፣ በትውልድ ልብ ላይ የሚታወሱ፡፡

አንዳንድ ቀናት አሉ ደስታ የበዛባቸው፣ ድርብ ተድላ የሚታይባቸው፣ ታሪክ የሚሠራባቸው፣ አንዳንድ ቀናት አሉ አደራ የሚሰጥባቸው፣ አደራ የሚቀበሉባቸው።

ጀግኖች ለሀገራቸው ቃል ይሰጧታል፤ ቃል ሰጥተው፣ በቃል ጸንተው፣ ደም ስትፈልግ ደማቸውን፣ አጥንት ስትፈልግ አጥንታቸውን፣ ሕይወት ስትፈልግ ሕይወታቸውን ይሰጧታል፡፡ በሞታቸው ያጸኗታል፤ በአጥንታቸው ያስከብሯታል፤ በደማቸው ያኮሯታል፡፡

ጀግኖች ለሀገራቸው ከስጦታዎች ሁሉ የላቀውን ስጦታ ይሰጧታል፡፡ ጀግኖች ከራሳቸው ይልቅ ሀገርና ሕዝብ ያስቀድማሉ፣ ሌላውን ለማኖር እነርሱ ይሞታሉ፣  ሌላውን ለማስከበር እነርሱ ዝቅ ይላሉ፣ ሌላውን ለማቆም እነርሱ ይወድቃሉ፣ ሌላውን አጥግቦ ለማሳደር እነርሱ ይራባሉ፣ ሌላው እንዳይጠማ እነርሱ ይጠማሉ፣ ሌላው እንዳይታረዝ እነርሱ ይታረዛሉ፣ ሌላው እንዳይንገላታ እነርሱ ይንገላታሉ፣ ሌላው እንዳይከፋው እነርሱ ይከፋሉ፣  ሌላው ምቾቱ እንዳይጎድልበት እነርሱ ድንጋይ ተንተርሰው ይተኛሉ፣ ጫማቸውን ሳያወልቁ በምሽግ ውስጥ ውለው ያድራሉ፡፡

ለሀገር ክብር ሐሩሩን፣ ብርድና ቆፈኑን፣ እሾህና አሜካላውን፣ የጦር ፍላጻውን ሁሉንም ይችላሉ፡፡ ስለ ሀገር ሲሉ ተድላና ምቾትን ይረሳሉ፡፡ መነሻቸው የሀገራቸው ፍቅር፣  መድረሻቸውም የሀገራቸው ክብር ነው፡፡ ከሀገር ፍቅር እና ከሀገር ክብር የዘለለ የጠራቸው፣ አስሮ ያኖራቸው፣ መከራና ስቃዩን፣ መቁሰል እና መድማቱን፣ መሞትና ማለፉን የሚያስታግሳቸው የለም፡፡  የሀገራቸው ፍቅር፣ የሠንደቃቸው ክብር ግን ሁሉንም አስረስቶ ለእርሷ፣ በእርሷ፣ ስለ እርሷ ያኖራቸዋል፡፡  

ሀገር የሚወደው ብርቱ ልጅ በአንድ ቀን ሁለት ቃል ኪዳን አሠረ፡፡  በአንድ ቀን ሁለት  ብርቱ ፣ እምነት፣ ጀግንነት፣ ጽናት፣ ቆራጥነት እና ፍጹም መልካምነት የሚፈልጉ ቃልኪዳኖችን አሠሩ፡፡  ነገሩ ግራ ሊያጋባ ይችላል፡፡ አንድ ቃል እንጂ ሁለት ቃል የለም የሚል አይጠፋም፡፡ እርሱ ግን ሁለት ትክክለኛ ቃል ኪዳኖችን፣ ሁለት ትክክለኛ ማተቦችን አሰረ እንጂ አንዱን አፍርሶ ሌላ ቃል አልገባም፡፡

ነገሩ ወዲህ ነው የኢፌዴሪ አየር ኀይል 88ኛ ዓመቱን የምሥረታ በዓል እያከበረ ነበር፡፡ ከምስረታው በዓል ጋርም የአየር ኀይል አካዳሚ ያሰለጠናቸውን ሰልጣኖችን ያስመርቃል፡፡ በዚህ ታላቅ ሥነ ሥርዓት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)፣ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው፣ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች፣ ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዦች ተገኝተዋል፡፡

ከተመራቂ ሰልጣኖች መካከል ደግሞ እጩ መኮንን ይበልጣል ማንደፍሮ አንደኛው ነው፡፡ እጩ መኮንን ይበልጣል ከዚህ ቀደም በአየር ኀይል አካዳሚ የቴክኒክ ኮሌጅ ተመርቋል፡፡ ዛሬ ደግሞ የእጩ መኮንንነት ስልጠናውን በብቃት አጠናቆ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የምክትል መቶ አለቃ ማዕረግ ለብሷል፡፡  ይህ ወታደር ከኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ ሥር ተንበርክኮ ቃል ኪዳኑን ለሀገር ሰጥቷል፡፡ በዚሁ ቀንም ለምትመስለው ለሚመስላት፣ ብታጣና ብትነጣ ላይለያት ቃል ለሚሰጣት የወደፊት ሚስቱ ቃል ኪዳን አስሯል፡፡

እጩ መኮንኑም  በፖለቲካው እና በወታደራዊ ዘርፍ ሀገሪቱን በሚመሩ ታላላቅ መሪዎች ፊት ከሀገሩ በተጨማሪ ለወደፊት ሚስቱ ቃል ኪዳን ሰጣት፡፡ አስቀድሞ ገና ለሀገሩ ቃሉን ሰጣት፣ ላይክዳት፣ ሊጠብቃት፣ ኮርቶ ሊያኮራት፣ ከጠላቶቿ ጋር ተዋድቆ ሊያስከብራት፣  የነጻነት እና የአሸናፊነት ታሪኳን ሊያስቀጥልላት፣ በጠላቶቿ ፊት ያላትን ግርማ ሞገስ ከፍ ከፍ ሊያደርግላት፣ ከአረንጓዴ ቢጫ ቀዩዋ ሠንደቅ ግርጌ ተንበርክኮ ቃል ኪዳኑን ሰጣት፡፡ ከራስ በላይ ለሕዝብ እና ለሀገር ብሎ ማለላት፡፡ ብከዳሽ ይክዳኝ፣ ብረሳሽ ይርሳኝ፣ ብተውሽ ይተወኝ ብሎ በልቡ ማሕተም አተመላት፡፡

ሀገሩ የምታምርበትን እና በዓለሙ ሁሉ ደምቃ የምትታይበትን፣ ዘመን የምትቆጥርበትን፣ ተስፋ የምትቀበልበትን፣ በረከት የምታገኝበትን ሠንደቋን ከፍ አደረገላት፡፡ አስቀጥሎም ሲደክመው ለምታበረታው፣ ልጆች ወልዳ ለምታስመው፣ ሀገር ወዳድ ልጆችን ለምትሰጠው፣ እንደ ራሱ አድርጎ ለሚወዳት፣ እንደራሱም አድርጎ ለሚያኖራት ፍቅረኛው በታላቅ ሥነ ሥርዓት ቃል ኪዳኑን ሰጥቶ ቀለበት አሠረላት፡፡

የቀለበት ሥነ ሥርዓቱን የተመለከቱት  የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) “ ጋብቻቸውን በዚህ ታሪካዊ ቀን ለፈጸሙ ሁለት ወጣቶች እንኳን ደስ አላችሁ፣ ጋብቻችሁ የሰመረ፣ ያማረ በልጆች ያበበ ለአየር ኀይል ቀን መታሰቢያ እንዲኾንላችሁ እመኛለሁ” አሏቸው፡፡

እጩ መኮንኑ ነገ ሊኾን የሚመኛቸው ጄኔራሎች እያጨበጨቡለት፣ የሀገሪቱ መሪዎች እያጀቡት፣ የጦር ጓዶቹ በወታደራዊ ሥነ ሥርዓት እያደመቁት፣ የጦር ሰልፈኞች በግራና በቀኝ ቆመውለት ቃል ኪዳኑን ፈጸመ፡፡

በአንድ ቀን ለሀገር እና ለሚስት ቃል መግባት፤ በአንድ ቀን ራስን አሳልፎ መስጠት፡፡ በአንድ ቀን ለሀገር እና ለትዳር መዘጋጀት፡፡ መልካም ትዳር፤ መልካም ሀገር ማገልገል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ከዓለም አቀፍ የኃይል አሰላለፍ እና ከዘመኑ የውጊያ አውድ አኳያ ኢትዮጵያ አየር ኃይሏን እንደምታዘምን ይታወቃል” ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ
Next articleበአማራ ክልል የገጠመውን ችግር ሙሉ በሙሉ በመቀልበስ የሕዝቡን ሰላም ለማረጋገጥ “የጣና ቃል ኪዳን ሰነድ” ስምምነት ተፈረመ።