
ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ) 88ኛ ዓመት የአየር ኃይል የምስረታ ቀን ማጠቃለያ መርሐ ግብር እየተካሄደ ነው፡፡ በመርሐ ግብሩ ላይ ላለፉት ዓመታት ወታደራዊ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ የአየር ኃይሉ አባላት ተመርቀዋል፡፡
በሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የሀገር መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ አየር ኃይሉ በለውጥ ሂደት ውስጥ እንደኾነ ጠቅሰዋል፡፡
የቀጣናችን ስትራቴጂክ ሁኔታ ሀገራችን ላይ ከሚኖረው ተፅዕኖ፣ ከዓለም አቀፍ የኃይል አሰላለፍ እና ከዘመኑ የውጊያ አውድ አኳያ ኢትዮጵያ አየር ኃይሏን፣ ባህር ኃይሏን፣ ምድር ጦሯን እና የሳይበር ኃይሏን ባልተቆራረጠ መልኩ እንደምታዘምን እና እንደምታሳድግ ይታወቃል ብለዋል፡፡
ባለፉት የለውጥ ዓመታት በተቋም ደረጃ በተካሄደ ሪፎርም ሁሉም ዘርፎች በአደረጃጀት፣ በሥነ ልቦና እና በትጥቅ በማዘመን የመፈጸም አቅሙን በከፍተኛ ደረጃ አሳድጓል፡፡ እስካሁን በተደረጉ የልውጥ ሂደቶች ታላቅ እምርታም ተገኝቷል፡፡
አየር ኃይሉ ከሀገራዊ እና ተቋማዊ ለውጡ በፊት የእድሜውን ያክል ለውጥ አልታየበትም ነበር ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ከለውጡ በኋላ በተለየ ትኩረት ለማዘመን ጥረት ተደርጓል ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!