“አየር ኀይል ለሀገር ሉዓላዊነት እና አንድነት በተለያዬ ጊዜ ወርቃማ ገድሎችን ፈጽሟል” ሌትናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ

34

ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የኢፌዴሪ አየር ኀይል 88ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል የማጠቃለያ ሥነ ሥርዓት እና የአየር ኀይል ሠልጣኞች የምረቃ ሥነ ሥርዓት እየተካሄደ ነው፡፡

በሥነ ሥርዓቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች እና ወታደራዊ መሪዎች ተገኝተዋል፡፡

በሥነ ሥርዓቱ ላይ መልእክት ያስተላለፉት የአየር ኀይል ዋና አዛዥ ሌናትናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ኢትዮጵያ ዘመናዊ የመንግሥት አደረጃጀት እና መንግሥታዊ ተቋማት ከገነቡ ጥንታዊ ሀገራት መካከል አንዷ መኾኗን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር ኀይል በተለያዩ መንግሥታዊ ሥርዓቶች እና ውጣ ውረዶችን ያለፈ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡

ለሀገር ሉዓላዊነት እና አንድነት በተለያዬ ጊዜ ወርቃማ ገድሎችን ፈጽሟልም ብለዋል፡፡

የአየር ላይ ነብሮች የተባሉ በራሪዎች ክቡር ሕይዎት ገብረዋል፣ ተሰውተዋልም ነው ያሉት፡፡

አየር ኀይል በቀላሉ የሚገነባ አለመኾኑን የተናገሩት አዛዡ በ1983 ዓ.ም በተደረገው የመንግሥት ለውጥ አየር ኀይሉ ፈርሶ ሠራዊቱም ተበትኖ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ይህ ደግሞ አየር ኀይሉን በብዙ አስርት ዓመታት ወደኋላ መልሶታል ነው ያሉት፡፡

አየር ኀይሉ ታሪኩን በጠበቀ መልኩ እንዳይከበር ኾኖ መቆየቱንም ገልጸዋል፡፡

በተካሄደው የማሻሻያ ሥራ ትርክቶችን በማረም ትክክለኛውን መረጃ ለማውጣት መቻሉንም ተናግረዋል፡፡

በተደረገው ጥናትም የአየር ኀይል የተመሠረተበት ቀን እንዲከበር መደረጉንም ገልጸዋል፡፡

የአቭየሽን ሥልጠናን መሸከም የሚችል የሰው ኀይል እንዲኖር መሠራቱንም ተናግረዋል፡፡

የአየር ኀይሉን የሰው ኀይል ፍላጎት ከማሟላት አልፈው ለጎረቤት ሀገራትም ድጋፍ እያደረጉ መኾናቸውን ነው የተናገሩት፡፡

በተቋሙ ከተካሄዱ ለውጦች መካከል ትጥቅን ማሻሻል መኾኑን የተናገሩት አዛዡ ትጥቆቹን ለግዳጅ ዝግጁ ማድረጋቸውንም ገልጸዋል፡፡

በጦርነት ሳይንስ ዘመኑን የዋጀ ትጥቅ እንደሚያስፈልግም አመላክተዋል፡፡

የአየር ኀይል የውጊያ መሠረተ ልማት መሠራቱንም አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር ኀይል የአፍሪካ ተቀዳሚ አየር ኀይል መኾኑንም ገልጸዋል፡፡

በሰው ኀይል፣ በትጥቅ እና በመሠረተ ልማት የተገነባው ግንባታ ኢትዮጵያን የሚዳፈር ጠላት ደግሞ ደጋግሞ እንዲያስብ የሚያደርግ ነውም ብለዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ሁሉም ለሰላም እንዲቆም ጠየቀ።
Next articleኢትዮጵያ አየር ኃይል እጩ መኮንኖችን፣ ቴክኒሻኖችንና አብራሪዎችን አስመረቀ።