
ባሕር ዳር፡ የካቲት 13/2012 ዓ.ም (አብመድ) ዘመንና ሥርዓት ያልፈቱት ታማኝነት!
ድርጊቱ የተፈጸመው በጎንደር ከተማ አስተዳደር ነው፡፡ ቢቢሲ በአፍሪካ ዓምዱ “ለ20 ዓመታት ጎረቤቴ ቤቴን እያከራዩ ሲጠብቁልኝ ቆይተዋል” በሚል ያስነበበውን ታሪክ ልናጋራችሁ ነው፡፡ ከ20 ዓመታት በፊት ኢትዮጵያና ኤርትራ ወደ ጦርነት መግባታቸውን ተከትሎ ኤርትራውያን ከኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያውያንም ከኤርትራ እንዲወጡ ተደረገ፡፡
በዚህ አግባብ ወይዘሮ ምግቤ ተመሥገን ከጎንደር ወደ ኤርትራ ለመሄድ ተገደዱ፡፡ ወይዘሮ ምግቤ ከኢትዮጵያ የመውጣት ፍላጎት ባይኖራቸውም የመንግሥታት ጠብ በወቅቱ ጉልበት ነበረውና ቤታቸውንና ጎረቤቶቻቸውን ትተው ሄዱ፡፡
በዚያ ቀውጢ ወቅት ወይዘሮ ሻሽቱ ንጉሤ የተባሉ ጎረቤታቸው አጽናንተው፤ ቤት ንብረታቸውን እንደሚጠብቁላቸው ቃል ገብተውና የመንግሥታቱ ግጭት ጊዜያዊ እንደሚሆን ተስፋ አድርገው ሸኟቸው፡፡ ወይዘሮ ሻሽቱ ቤቱን እያከራዩ ገንዘቡን እያስቀመጡላቸው ለዓመታት በታማኝነታቸው ቀጠሉ፡፡ በታችኛው የመንግሥት መዋቅር ባሉ ሰዎች ጭምር ተጽእኖ ቢደረግባቸውም “አደራ አለብኝ!” ብለው በአቋማቸው ፀኑ፡፡
በመጨረሻም ከ20 ዓመታት በኋላ ኢትዮጵያና ኤርትራ ፍቅር አወረዱ፤ ድንበሮቻቸውንም ከፈቱ፡፡ ወይዘሮ ምግቤም ወደ ጎንደር የጎረቤታቸውን አደራ ጠባቂነት ተስፋ አድርገው መጡ፤ ተስፋ እንዳደረጉትም ቤታቸው እስከ ሙሉ ክብሩና ኪራዩ ጠበቃቸው፡፡
“በጎረቤታቸው ታማኝነት በእጅጉ የተደሰቱት ኤርትራዊትም ‘ከእንግዲህ ሞቴን ጎንደር ያድርገው!’ ብለው ኑሯቸውን በዚያው አደረጉ” ብሏል ቢቢሲ በድረ ገጹ፡፡
አብመድ ከዚህ ቀደምም በርካታ ኢትዮጵያውን በጎንደር፣ በባሕር ዳርና በደብረ ማርቆስ በተመሳሳይ የኤርትራውያንን ቤት ጠብቀውና ኪራያቸውን በባንክ አስቀምጠው አደራቸውን መወጣታቸውን ዘግቧል፤ በባሕር ዳር ከ20 ዓመታት በፊት እቁብ ሲጥሉ አቋርጠው የሄዱ ኤርትራዊን ገንዘብ በባንክ እስከ ወለዱ አስቀምጠው ያስረከቡ ታማኞችንም አስተዋውቀናችሁ ነበር፤ መታመን ትልቅነት ነው፡፡
መልካም ቀን!
በአብርሃም በዕውቀት