የአየር ኃይል አብራሪ በመኾን የሚወዷትን ኢትዮጵያን በማገልገል ትልቅ ታሪክ ለመሥራት እንደሚፈልጉ የአየር ኃይል አካዳሚ የበረራ ሠልጣኞች ተናገሩ።

33

ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ጥቁር አንበሳ የአየር ትርዒት ብቃት ያለው አብራሪ በመኾን ሀገርን ለማገልገል ተነሳሽነት ፈጥሮብናል ብለዋል ሠልጣኞቹ።

ጥቁር አንበሳ የአየር ትርዒት ሙያዊ ብቃት በማዳበር የኢትዮጵያን አየር ክልል ለመጠበቅ ላላቸው ዓላማ ስንቅ መኾኑንም የኢትዮጵያ አየር ኃይል አካዳሚ የበረራ ሠልጣኝ ተማሪዎች ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል 88ኛ ዓመት የምስረታ በዓል የማጠቃለያ ሥነ-ሥርዓት ዛሬ በቢሾፍቱ አየር ኃይል ጠቅላይ መምሪያ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

በመርሐ-ግብሩ “ጥቁር አንበሳ” የተሰኘ የአየር ትርዒት የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች አየር ኃይል አባላት ከኢትዮጵያ አየር ኃይል ጋር በመኾን አከናውነዋል።

ሠልጣኞቹም የአየር ትርዒቱ የአየር ኃይል አብራሪነት የሚፈልገውን የሙያ ብቃት በማጎልበት ሀገራቸውን በከፍተኛ ሙያዊ ኃላፊነት ለማገልገል መነሳሳት እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል።

በአካዳሚው የሁለተኛ ዓመት የበረራ ተማሪ የኾነችው ካዴት መርሰን ግርማ፤ ትርዒቱ ልብን የሚያሞቅና ደስ የሚያሰኝ ስሜት እንደፈጠረባት ገልጻለች።

ትርዒቱ ተግቶና ጠንክሮ በመሥራት ሀገርን ማገልገል እንደሚቻል ትምህርት ወስጄበታለሁ ብላለች።

በኢትዮጵያ የሴት አየር ኃይል አብራሪዎች በብዛት እንደማይገኙ ገልጻ ትምህርቷን አጠናቅቃ አብራሪ በመኾን ለሌሎች እንስቶች አርዓያ መኾን እንደምትፈልግ ተናግራለች።

የአንደኛ ዓመት የበረራ ተማሪ የኾነው ካዴት ጫላ ጉቱ በበኩሉ፤ በትርዒቱ የተመለከተው ነገር ሀገሩን ለማገልገል ይበልጥ ተነሳሽነት እንደፈጠረበት ገልጿል።

የአየር ኃይል አባል በመሆኑ ኩራት እንደሚሰማው ገልፆ፤ ወደፊት የአየር ኃይል አብራሪ ለመኾን ሕልሙን ለማሳካት በትጋት እንደሚሰራ ተናግሯል።

ሌላኛዋ የበረራ ተማሪ ካዴት ሐና ግርማ፤ በትርዒቱ አንድ ሰው ዓላማውን ለማሳካት ከተጋ ጥሩ ደረጃ ላይ መድረስና ስኬታማ መሆን እንደሚችል የተማርኩበት ነው ብላለች።

ሌላኛው የኢትዮጵያ አየር ኃይል አካዳሚ የበረራ ተማሪ የሆነው ካዴት በፍቃዱ ዓለማየሁ፤ ወታደር መኾን የዓላማ ጽናትና ሀገርን መውደድ አጣምሮ የሚሰጥ ሙያ መኾኑን ገልፆ፤ ወታደርም አብራሪም መኾን ልዩ ስሜት እንደሚፈጥር ተናግሯል።

ትምህርቱን ጠንክሮ በመማር አገሩን ለማገልገል ዝግጁ ነኝ ብሏል።

ካዴት ሐና ግርማ እና ካዴት ጫላ ጉቱ የአየር ኃይል አብራሪ በመኾን የሚወዷትን ኢትዮጵያን በማገልገል ትልቅ ታሪክ ለመሥራት እንደሚፈልጉ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የአየር ኃይሉ 88ኛ ዓመት የምስረታ በዓል “በመስዋዕትነት ሀገርን የዋጀ፤ የኢትዮጵያ አየር ኃይል” በሚል መሪ ኃሳብ ከኅዳር 20 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ እየተከበረ ይገኛል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleለክልሉ ሰላም መስፈን የሁሉም ኅብረተሰብ አስተዋጽኦ እንደሚያስፈልግ የሰቆጣ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።
Next articleየአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ሁሉም ለሰላም እንዲቆም ጠየቀ።