
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል መንግሥት የክልሉን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እና ሰላም ለማስጠበቅ የሰላም ጥሪ ካቀረበ ሦሥተኛ ቀኑን አስቆጥሯል።
ይህንን የሰላም ጥሪ በማስመልከት ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉት የሰቆጣ ከተማ ነዋሪዎች ከእርቀ ሰላም ትርፍ እንጂ ኪሳራ የለውም ብለዋል።
የሰቆጣ ከተማ ነዋሪው አቶ ሞገስ ገብሬ “በመቻቻል እና በመደማመጥ ከኖርን እኛ ኢትዮጵያዊያን ለዓለም የሚተርፍ ጸጋ አለን፤ እርስ በርስ ካልተደማመጥን ግን የኛን መውደቅ ለሚጠብቁ ጠላቶቻችን ምቹ ሁኔታን እንፈጥራለን” ነው ያሉት።
የሰላምን ዋጋ ባለፉት ዓመታት አይተነዋል ያሉት አቶ ሞገስ ሰላምን መጠበቅ እና ማስጠበቅ የመንግሥት ብቻ ሳይኾን የሁሉም ኢትዮጵያዊ ግዴታ እንደኾነም አስረድተዋል።
መምህርት አዲስ መኳንንትም “የአማራ ክልል ሰላም መኾን ለመላው ኢትዮጵያ ሰላም መኾን ወሳኝ በመኾኑ መላው ኢትዮጵያዊ ለክልሉ ሰላም መኾን እገዛ ሊያደርግ ይገባል” ነው ያሉት፤ ሀገር የምትለማው ሕዝቦቿ በሰላም ሲኖሩ ነው ያሉት መምህርት አዲስ የተለየ ሃሳብ ሲኖር በመነጋገር ችግርን መፍታት ባሕል ሊኾን እንደሚገባ ተናግረዋል።
ዲያቆን አደራጀው ጌታወይ እንደ ሃይማኖትም፣ እንደ ሰብዓዊነትም ቢኾን ሰላም የሚጠላ አይደለም ነው ያሉት።
ለክልሉ ሰላም መስፈን የሁሉም አስተዋጽኦ ያስፈልጋል ያሉት ዲያቆን አደራጀው ልዩነትን በምክክር ለመፍታት ሁሉም ሊሠራ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ዘጋቢ፡- ደጀን ታምሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!