“የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች እያበረከቱት ለሚገኘው ልዩ አስተዋፅኦ የክልሉ መንግሥት ታላቅ ምስጋና ያቀርባል” የአማራ ክልል መንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ

37

ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል መንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ በማኅበራዊ ትሥሥር ገጹ ባስተላለፈው መልእክት፤ መንግሥት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ ውጤታማ ፍጻሜ እንዲኖረው ለማስቻልና ደም አፋሳሽ ግጭቶች በውይይትና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ብቻ እንዲፈቱና ክልላችን ከግጭት አዙሪት እንዲወጣ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች እያበረከቱት ለሚገኘው ልዩ አስተዋፅኦ የክልሉ መንግስት ታላቅ ምስጋና ያቀርባል ብሏል።

ሙሉ መልእክቱ ቀጥሎ ቀርቧል፦

አንድ ሀገር፤ አንድ ኅልውና እና ተመሳሳይ ራዕይ ያለን አንድ ሕዝብ በመሆናችን ከሰላም የተሻለ የሚበጀንም ሆነ የሚያዋጣን አማራጭ የለም !!

በሰሜን ኢትዮጵያ የሀገር ሉዓዋላዊነትንና የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ሲባል በፌደራል መንግስት የበላይ መሪነት በተመራው ዘመቻ ከሌሎች እህት ወንድም ሕዝቦች ጋር በጋራ በመሆን የአማራ ክልል ሕዝብ እንደ ሕዝብ ሁሉን አቀፍ መስዋእትነት መክፈሉን ገልጿል፡፡

በዘመቻውም ከፍተኛ ሰብዓዊ መስዋእትነት እና በግማሽ ትሪሊየን ብር የሚገመት ቁሳዊ ጉዳት የደረሰበት ስለመሆኑ ተዓማኒነት ያላቸው በርካታ በጥናት የተደገፉ ማስረጃዎች ይፋ መሆኑ ይታወሳል፡፡

ክልላችን ከሰሜኑ ጦርነት ጉዳት ለማገገም የሚችልበት በቂ ግዜ ሳያገኝ መልክና ይዘታቸውን የቀየሩ፤ ተከታታይ ግጭቶች ውስጥ ሲባጅ ከርሟል፡፡ ሁለንተናዊ ዋጋም ከፍሏል፤ እየከፈለም ይገኛል፡፡

የግጭቱ አዙሪትም እንደ አንድ ማኅበረሰብ ክፉኛ ፈትኖታል፡፡ ካሳለፍነው የበለጠ አስከፊ የሰብዓዊ፤ ስነ-ልቦናዊ፤ አካላዊ፤ ኢኮኖሚያዊ፤ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ስብራትን ሊያስከትል የሚችልበት መሆኑ አጠያያቂ አይደለም፡፡

በመሆኑም የአማራ ክልል መንግሥት በክልሉ ሕዝብ ላይ ተጨማሪ የሰብዓዊ፤ ስነ-ልቦናዊ፤ አካላዊ፤ ኢኮኖሚያዊ፤ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳቶች እንዳይባባሱ ለማድረግ ከአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ጋር ባደረገው ውይይት በክልላችን ውስጥ በሚታዩት በጦር መሣሪያ የታገዙ ግጭቶች ውስጥ ተሳትፎ ለነበራቸው ዜጎች ሁሉ ለ 7 ተከታታይ ቀናት የሚቆይ የሠላም ጥሪ አቅርቧል፡፡

ይህንን የሰላም ጥሪ መላው የክልላችን ሕዝብ በአዎንታዊ ጎኑ ተቀብሎ ደስታውን በተለያዩ መድረኮች ላይ ከመግለጹም ባሻገር ለተፈጻሚነቱ ከመንግስት ጎን ተሰልፎ የበኩሉን ገንቢ አስተዋጽዖ ለማበርከት ፍቃደኛነቱን አረጋግጧል።

መንግሥት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ ውጤታማ ፍጻሜ እንዲኖረው ለማስቻልና ደም አፋሳሽ ግጭቶች በውይይትና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ብቻ እንዲፈቱና ክልላችን ከግጭት አዙሪት እንዲወጣ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች እያበረከቱት ለሚገኘው ልዩ አስተዋፅኦ የክልሉ መንግሥት ታላቅ ምስጋና ያቀርባል።

ያለፍንባቸው አሳዛኝ የግጭት መንገዶች ራሳቸውን እየደገሙ የሚያንገላቱን እንዳይሆኑና ራስን የማድማት አውዳሚ ጉዞ እዚህ ላይ እንዲገታ ሁሉም በትጥቅ የተደገፈ ግጭት ተሳታፊ መንግስት የከፈተውን የሰላም በር እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም ለሰላም፤ ለውይይት እና ለአንድነት እድል እንዲሰጡ አበክረን እንጠይቃለን።

በእርግጥም አንድ ሀገር፤ አንድ ኅልውና እና ተመሳሳይ ራዕይ ያለን አንድ ሕዝብ እንደመሆናችን መጠን የሚበጀንም ሆነ የሚቀለን አማራጭ ይኽው የሠላም አማራጭ ብቻ ነው፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ጥቁር አንበሳ የአየር ትርኢት ኢትዮጵያና የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች በጋራ ለመሥራት ያላቸውን ጽኑ ፍላጎት በግልጽ ያሳየ ነው” ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ
Next articleበእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ “አየተሞገሰች ያለችው ዳኛ “ርብቃ ዌልች”