“ጥቁር አንበሳ የአየር ትርኢት ኢትዮጵያና የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች በጋራ ለመሥራት ያላቸውን ጽኑ ፍላጎት በግልጽ ያሳየ ነው” ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ

27

ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ጥቁር አንበሳ የአየር ትርኢት ኢትዮጵያና የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች በሁለትዮሽና ቀጣናዊ ጉዳዮች በጋራ ለመሥራት ያላቸውን ጽኑ ፍላጎትና ትብብር በግልጽ ያሳየ መሆኑን የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ገለጹ።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል 88ኛ ዓመት የምስረታ በዓል የማጠቃለያ ሥነ-ሥርዓት በቢሾፍቱ ከተማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

በሥነ-ሥርዓቱ የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች አየር ኃይል አባላት ከኢትዮጵያ አየር ኃይል ጋር በመሆን “የጥቁር አንበሳ የአየር ትርዒት” አሳይተዋል።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ የአየር ትርኢቱን አስመልክተው ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸው ኢትዮጵያና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በፖለቲካውም በውትድርናውም መስክ መልካም ግንኙነት ያላቸው ወዳጅ ሀገራት መሆናቸውን አንስተዋል።

በዚህም የጋራ አቅምን አስተባብሮ በመጠቀምና ልምድ በመለዋወጥ ረገድ ውጤታማ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ገልጸዋል።

ዛሬ በሁለቱ ሀገራት አየር ኃይሎች ስኬታማ የአየር ትርኢት ማሳየት መቻሉ የትብብር ሥራው ማሳያ ነው ብለዋል።

በስኬት የተከናወነውን “የጥቁር አንበሳ የአየር ትርዒት” በማስፋት በዓለም ከታወቁ የአየር ትርኢቶች ተርታ ለማሰለፍ እንደሚሠራም ተናግረዋል።

ለዚህም በርካታ ሀገራት ፍላጎት ያላቸው መሆኑን በመጥቀስ ሰሞኑን በተካሄደው የአፍሪካ አየር ኃይል አዛዦች ፎረም ላይ ለዚህ አጋዥ የሆኑ ሥምምነቶች መደረጋቸውን ጠቁመዋል።

በፎረሙ የአፍሪካ ሀገራት ለመተጋገዝና መሰረተ ልማቶችን በጋራ ለመጠቀም በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ መግለጻቸውን አንስተዋል።

ከዚህም ባሻገር የኢትዮጵያ አየር ኃይል አካዳሚ አቅም የማሳደግ ሥራ በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል።

የተለያዩ አፍሪካ ሀገራት የሥልጠና ፍላጎት ያላቸው በመሆኑ ይህንን ታሳቢ ያደረጉ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል 88ኛ ዓመት የምስረታ በዓል “በመስዋዕትነት ሀገርን የዋጀ የኢትዮጵያ አየር ኃይል” በሚል መሪ ኃሳብ ከሕዳር 20 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ እየተከበረ ይገኛል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በኢትዮጵያና በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች አየር ኃይሎች በጋራ የቀረበው ወታደራዊ የአየር ላይ ትርዒት በትብብር ከሠራን የምንደርስበትን ደረጃ ያሳየ ነው።” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
Next article“የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች እያበረከቱት ለሚገኘው ልዩ አስተዋፅኦ የክልሉ መንግሥት ታላቅ ምስጋና ያቀርባል” የአማራ ክልል መንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ