በየአካባቢያቸው ታጥቀው የወጡ አካላት ለሰላም ጥሪዉ ተገዥ እንዲኾኑ እንደሚሠሩ የሃይማኖት አባቶች ገለጹ፡፡

53

ጎንደር: ታኅሳስ 6/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል የተፈጠረውን የሰላም እጦት ወደነበረበት ሰላም ለመመለስ ከሰሞኑ የክልሉ መንግሥት የሰላም ጥሪ ማድረጉ ይታወቃል።

ይህን ተከትሎም የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ከወረዳዎች ከተወጣጡ የሃይማኖት አባቶች ጋር የበኩላቸውን ሚና በሚወጡበት ተግባር ዙሪያ ውይይት አድርጓል።

በውይይቱ ሃሳባቸውን ያጋሩ የሃይማኖት አባቶች የትኛውም ሃይማኖት ጥላቻ፣ ጦርነትን እና መገዳደልን አጥብቆ ያወግዛል ብለዋል።

የሃይማኖት አባቶቹ የነብስ ልጆቻቸዉ ሰብዓዊ ጉዳት በሚፈጥሩ ግጭቶች ውስጥ እንዳይገቡ አበክረዉ እንደሚመከሩ እና እንደሚገስጹ አንስተዋል።

የሰው ልጅን መግደል ፈጣሪ አምርሮ የሚጠላዉ በመኾኑ ከመገዳደል እና መሰል ተግባር መቆጠብ ያስፈልጋል ብለዋል።

የእርስ በርስ ጦርነት የራስ ሃብትን የሚያወድም በመኾኑም ችግሩን በውይይት መፍታት እንደሚያስፈልግ ነው ያነሱት።

የክልሉ መንግሥት ባስተላለፈው የሰላም ጥሪ ደስተኛ መኾናቸውን ያነሱት የሃይማኖት አባቶቹ በየወረዳዎቻቸው ታጥቀው የወጡ አካላት ለሰላም ጥሪው ተገዥ እንዲኾኑ እንደሚሠሩም አንስተዋል።

የሰላም ንግግሩ ፍሬያማ እንዲኾን ተቀራርቦ መነጋገር እንደሚያስፈልግ ከታጠቁ ኃይሎች አባላት መስማታቸውንም የሃይማኖት አባቶቹ አስረድተዋል።

ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ መንግሥት ከታጠቁ ኃይሎች ጋር መነጋገር፣ የሃይማኖት አባቶችም ምዕመኑን ማስተማር እና መምከር ያስፈልጋል ነው ያሉት።

በቀጣይም የተሰጣቸዉን ኅላፊነት በአግባቡ እንደሚወጡ የሃይማኖት አባቶቹ አንስተዋል።

በተፈጠረዉ የሰላም እጦት መንገዶች ተዘግተዉ ቆይተዋል ያሉት የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ወርቁ ኃይለማርያም በዚህም ዜጎች ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰዉ ለመሥራት ተቸግረዋል ነው ያሉት።

በክልሉ የተፈጠረውን የሰላም እጦት ወደነበረበት የተረጋጋ ሁኔታ ለመመለስ ክልሉ የሰላም እና የምህረት ጥሪ ማድረጉን ለሃይማኖት አባቶች ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በወንጀል ተጠርጥረው ጫካ ለገቡ ሁሉ መንግሥት የምህረት ጥሪ ማድረጉን ያነሱት አቶ ወርቁ የታጠቁ ኃይሎች እድሉን እንዲጠቀሙበት የሃይማኖት አባቶች እንዲሠሩ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ከዚህ ቀደም 200 የሚኾኑ ታጣቂዎች የተሃድሶ ስልጠና መሰጠቱ የተነሳ ሲኾን የሰላም ጥሪ ከተደረገ ወዲህ ደግሞ በርካታ ወገኖች በምህረት ጥሪ ገብተዋል ተብሏል።

በቀጣይም ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ሁሉም አካል የበኩሉን እንዲወጣ ተጠይቋል።

ዘጋቢ፡- አዲስ ዓለማየሁ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየግብርና ሚኒስቴር 400 ሺህ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የውኃ መሳቢያ ፓምፕ ድጋፍ አደረገ።
Next article“በኢትዮጵያና በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች አየር ኃይሎች በጋራ የቀረበው ወታደራዊ የአየር ላይ ትርዒት በትብብር ከሠራን የምንደርስበትን ደረጃ ያሳየ ነው።” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ