ሰላም ለገቢ ሥራ እስትንፋስ በመኾኑ የሰላም ጥሪዉ ለገቢ ሥራ መሻሻል አይነተኛ ሚና እንደሚኖረው የገቢዎች ቢሮ ገለጸ።

21

ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የገቢ ሥራ ውጤታማነት የመጀመሪያው መለኪያ ሰላም ነው ያለው የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ አልፎ አልፎ ችግሮች ቢኖሩም ሰላም በነበረበት በ2015 በጀት ዓመት እንደ ክልል የዕቅዱን 88 ነጥብ 8 በመቶ መሠብሠብ መቻሉን ገልጿል። በ2015 በክልሉ 42 ነጥብ 85 ቢሊዮን ብር ለመሠብሠብ ዕቅድ ተይዞ 38 ነጥብ 06 ቢሊዮን ብር መሠብሠብ መቻሉንም አስታውቋል።

በአንፃሩ በ2016 በጀት ዓመት እንደ ክልል በርካታ የሕዝብ ጥያቄዎችን ለመመለስ ታሳቢ ተድርጎ 71 ነጥብ 65 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ቢታቀድም ክልሉ በገጠመው የሰላም እጦት ምክንያት እንደልብ በመንቀሳቀስ ግብር መሠብሠብ አለመቻሉን ነው የገለጸው፡፡

ቢሮው ምንም እንኳን ችግሮች ቢያጋጥሙትም በችግር ውስጥ እያለፈ እስካሁን 13 ቢሊዮን ብር መሠብሠብ ችለናል ነው ያለው፡፡ ይህም የዕቅዱን 18 ነጥብ 14 በመቶ ማለት ነው።

ከዓመታዊ ዕቅዱ አንፃር በሩብ ዓመቱ 13 ቢሊዮን ብር መሠብሠብ ችለናል ብሏል ገቢዎች ቢሮ፡፡ ይህም የዕቅዱን 72 ነጥብ 57 በመቶ ብቻ ሲኾን ይህም የኾነው በሰላም ችግር እንደኾነ ቢሮው ገልጿል፡፡

ቢሮው እንዳለው መንግሥት ያስተላለፈው የሰላም ጥሪ ለገቢ ሥራ መሻሻል አይነተኛ ሚና እንደሚኖረው በማመን ጥሪው ተገቢ እና ትክክል በመኾኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው ነው፡፡

በወንድማማቾች መካከል የሚፈጠርን ግጭት ለማብረድ መንስዔውን መሠረት ያደረገ ጥልቅ ውይይት፣ ምክክር፣ እና መነጋገር እንደኾነም ቢሮው አስገንዝቧል።

ጥሪው ፍሬ አፍርቶ በክልሉ ሙሉ በሙሉ ሰላም ከሠፈነ ገቢን በአግባቡና በፍትሐዊነት በመሠብሠብ ሕዝቡ የሚያነሳቸውን የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ እንደማይቸገርም የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ገልጿል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የኢትዮጵያ አየር ኃይል የሠው አልባ የአየር ምድብን መርቀው ከፈቱ።
Next articleየግብርና ሚኒስቴር 400 ሺህ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የውኃ መሳቢያ ፓምፕ ድጋፍ አደረገ።