
ባሕር ዳር: ታኅሳስ 6/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል መንግሥት ያስተላለፈውን “የሰላም ጥሪ” በተመለከተ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ነዋሪ ሴቶች ውይይት አድርገዋል።
የአማራ ክልል መንግሥት ግጭትን ትተው ሰላምን ለሚመርጡ አካላት የሰላም ጥሪ ማስተላለፉ ይታወሳል። ከባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የተውጣጡ ሴቶችም የሰላም ጥሪው ተግባራዊ በሚኾንበት ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል።
በውይይቱም ሴቶች ሰላምን ለማረጋገጥ ሚናቸው ላቅ ያለ መኾኑ ተመላክቷል። ክልሉ ከገባበት ቀውስ ለመውጣት ሰላማዊ አማራጮችን መጠቀም እንደሚገባም ተገልጿል። በውይይቱ የተገኙ ሴቶች የችግር ገፈት ቀማሾች መኾናቸውንም ተናግረዋል። የወንድማማቾች ግድያ ቆሞ ሰላማዊ አማራጮችን መጠቀም ይገባልም ብለዋል።
ሰላም ለአንድ ወገን ብቻ ሳይኾን ለሁሉም አስፈላጊ መኾኑን ተናግረዋል። የሕዝብ ጥያቄዎችን በሰላማዊ መንድ መፍታት እንደሚገባም ገልጸዋል። ክልሉን ሰላማዊ እናድርግ ከተባለ ሁሉም ለሰላም እጁን መዘርጋት ይገባዋልም ብለዋል። የሰላም ጥሪውን መቀበል ክልሉን ሰላማዊ እንደሚያደርገውም ተናግረዋል።
እናቶች በተቻለ መጠን የመምከር ሚናቸውን እና ልጆቻቸውን የማረቅ ሥራ እንደሚሠሩም ተናግረዋል። ሀገርን በፖሮፓጋንዳ እና በውሸት እያናጉ ሕዝብን ሰላም መንሳት እንደማይገባም ገልጸዋል። የሰላም እጦት የኑሮ ውድነትን በማባባስ ሕይዎታቸውን ከባድ እንዳደረገባቸውም ተናግረዋል። የሰላም ጥሪውን መቀበል እና ለሰላም ተገዢ መኾን ሕዝብን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም አመላክተዋል።
መንግሥት ያደረገው “የሰላም ጥሪ” ሰላምን ለማምጣት ጥሩ እርምጃ መኾኑንም ገልጸዋል። የሕዝብ ስቃይ እና መከራ ሊበቃ እንደሚገባም ጠይቀዋል። የእናቶችን እንባ እና ሰቆቃ ለማስቆም ሰላማዊ አማራጮችን መጠቀም ይገባል ነው ያሉት። ወላጆች የሰላም ሚናቸውን መወጣት እንደሚገባቸውም አመላክተዋል። የአሉባልታ ወሬ እና የሽብር ዘመቻ ዋጋ እያስከፈለ መኾኑንም ገልጸዋል።
የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ሴቶች ሕጻናት፣ ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ሰብለ ዘውዱ ለኑሮ ውድነት መቀነሥ እና የሥራ እድልን ለመፍጠር ሰላም ወሳኙ ጉዳይ መኾኑንም ተናግረዋል። የሰላም ጥሪውን መተግበር ለምንጠይቃቸው ጥያቄዎች ሁሉ ምላሽ ያመጣል ነው ያሉት። ማታ ማታ ነውጠኛ ቀን ቀን ሰላም መፈለግ እንደማይገባም አመላክተዋል።
ለዘላቂ እና ለእውነተኛ ሰላም ከንግግር ያለፈ ሥራ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል። እናቶች ከሁሉም በበለጠ ልጆቻቸውን የመምከር እና ከጥፋት የመመለስ እድል እንዳላቸውም ተናግረዋል። ሴቶች ተናግረው የማሳመን ሚናቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።
እርስ በእርስ በመገዳደል የሚሳካ ነገር እንደማይኖርም ተናግረዋል። ሴቶች ባሎቻቸውን፣ ልጆቻቸውን እና የአካባቢውን ማኅበረሰብ ለሰላም የማሳመን ሚናቸውን እንዲወጡም ተጠይቋል። የሰላም ጥሪው እንዲሳካ እና የቀረችውን ቀን ለመጠቀም ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባልም ብለዋል።
ለአማራ ሕዝብ የሚቆረቆር ሁሉ ሰላምን በማስቀደም የሕዝብ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚገባውም አመላክተዋል። የውስጥ እንደነትን በማጠናከር የሕዝብን ጥያቄ መመለስ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አሠራቴ ሙጨ የሰላም እጦቱ የኑሮ ውድነቱን አሳሳቢ እንዳደረገው ገልጸዋል። ሰላምን ማረጋገጥ እስካልቻልን ድረስ የኑሮ ውድነት አስቸጋሪነቱ ከፍ እያለ ይቀጥላል ነው ያሉት። የኑሮ ውድነቱን ለመቀነስ እና የተመቻቸ ኑሮ ለመኖር ሁሉም ለሰላም መሥራት ይገባዋልም ብለዋል።
ሴቶች ሰላምን የማምጣት እና ግጭትን የማርገብ ጥበብ እንዳላቸውም ገልጸዋል። የሕዝብ ጥያቄ የሚፈታው እርስ በእርስ በመግባባት እና በአንድነት እንጂ እርስ በእርስ በመገዳደል አይደለም ነው ያሉት። ለሰላም ግጭትን በቃ ማለት ይገባልም ብለዋል።
አንድ መኾን ካልተቻለ ክልሉንም ራሳችንም እናዋርዳለን፣ አንድ ከኾንን ግን እንከበራለን ነው ያሉት። መከባበር እና መተጋገዝ ከሌለ ጥያቄዎችን ለመፍታት አስቸጋሪ እንደሚኾንም ተናግረዋል። የሰላም ጥሪውን ከልብ በመውሰድ፣ የሰላም ባለቤት በመኾን ሌሎችም የሰላም ባለቤት እንዲኾኑ መሥራት ይገባል ነው ያሉት።
በየአካባቢው ያለውን ሕገ ወጥነት በጋራ መከላከል ይገባልም ብለዋል። ሌብነትን፣ መገዳደልን እና ግጭት መጥመቅን ነውር ነው ብሎ መነሳት ይገባል ብለዋል። ሁሉም ሴቶች ለሰላም ዘብ እንዲቆሙም ጥሪ አቅርበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
