
አዲስ አበባ: ታኅሳሥ 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ የባለአክሲዮኖች 19ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔን በአዲስ አበባ እያካሄደ ነው።
በጉባዔው እ. ኤ. አ የ2022/2023 የባንኩ ዓመታዊ ሪፖርት ቀርቧል።
ባንኩ ያጋጠሙትን ዓለምአቀፋዊ እና ሀገራዊ የፋይናንስ ችግሮችን በመቅረፍ ውጤታማ መኾኑን አስታውቋል።
ሪፖርቱን ያቀረቡት የአንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር ዓለም አስፋው የባንኩ አጠቃላይ ሃብት 35 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲኾን የተከፈለ የካፒታል መጠኑም 2 ነጥብ 63 ቢሊዮን ብር እንደኾነ ተገልጿል።
በተገባደደው በጀት ዓመት ባንኩ ያልተጣራ ጠቅላላ ትርፍ 747 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር ማግኘትም ችሏል።
በሃብት አሰባሰብ ረገድ የባንኩ አጠቃላይ ተቀማጭ ገንዘብ 27 ነጥብ 31 ቢሊዮን ብር ደርሷል። በበጀት ዓመቱም 4 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ ሠብሥቧል።
በዚህም አንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ በበጀት ዓመቱ 2 ነጥብ 26 ቢሊዮን ብር ብድር የሰጠ ሲኾን አጠቃላይ የብድር ክምችት መጠኑንም 28 ነጥብ 27 አድርሷል።
በተመሳሳይ በ2022/2023 የበጀት ዓመት 2 ነጥብ 82 ቢሊዮን ብር ብድር ተመላሽ አድርጓል።ይህም ጥሩ አፈጻጸም የታየበት እና ከባለፈው ዓመት የ46 በመቶ ብልጫ እንዳለው በሪፖርቱ ቀርቧል።
በዚሁ የበጀት ዓመት ባንኩ ትኩረት ሰጥቶ የሠራበት የውጭ ምንዛሬ ዘርፍ ሲኾን 54 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ማግኘትም ችሏል።
በተጨማሪም አዳዲስ ደንበኞችን ከማፍራት አንጻር 162 ሺህ አዲስ የሂሳብ ደብተር የከፈቱ ሲኾን በአጠቃላይ የደንበኞችን ቁጥር 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ደርሷል።
ባንኩ በአጠቃላይ 288 ቅርንጫፎች በመላው ኢትዮጵያ እንዳሉት ሲገለጽ ከዚህ ውስጥ 10 በተያዘው በጀት ዓመት የተከፈቱ ናቸው።
የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበሩ ዓለም አስፋው እንደገለጹት በበጀት ዓመቱ በኢኮኖሚው ላይ ተግዳሮት የነበሩ ዓለምአቀፍ እና ሀገር አቀፍ ክስተቶች ለባንክ ዘርፉም ከፍተኛ ጫና ፈጥሯል ብለዋል።
በተለይም በሰሜኑ ጦርነት ሥራ አቁመው የነበሩ ባንኮችን ሥራ ማስጀመር እና የአስቀማጭ ደንበኞች የጥሬ ገንዘብ ፍላጎት መጨመር የአንበሳ ባንክ ፈተና እንደነበሩ ገልጸዋል።
በተመሳሳይ በጦርነቱ ምክንያት ተበዳሪ ደንበኞችን ብር በወቅቱ መሠብሠብ አለመቻሉ የባንኩ ጤነኛ ያልኾነ የብድር መጠን እንዲጨምር አድርጓል ብለዋል።
ከነበሩት ቅርንጫፎችም እስከ አሁን ሥራ ያልጀመሩ 10 ቅርንጫፎች እንዳሉም ሊቀመንበሩ ገልጸዋል።
ሆኖም ባንኩ ያጋጠሙትን ችግሮች ለመቅረፍና ወደ ተሻለ ደረጃ ለመጓዝ የአምስት ዓመት ስትራቴጂ እቅድ ነድፎ ወደ ሥራ ገብቷል።
በዚህም ከባለፈው በጀት ዓመት አኳያ የተሻለ አፈጻጸም በማሳየት ከግብር በፊት 747 ሚሊዮን ብር አስመዝግቧል።
በባንክ ቴክኖሎጂ ዘርፍም የካርድ፣ የሞባይል እና የኢንተርኔት ባንኪንግ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል።
በተጨማሪም የአገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመን እየተጠቀመበት ያለውን የኮር ባንኪንግ ቴክኖሎጂ የማጎልበት ሥራም ማጠናቀቁን ሊቀመንበሩ አስታውቀዋል።
በቀጣይም የደንበኞች እርካታ ቁጥር መጨመር እንዲሁም ዘመኑን የሚዋጁ ቴክኖሎጂዎችን ጥቅም ላይ ለማዋል ጠንክሮ ይሠራል ተብሏል።
የባንኩን የተከፈለ ካፒታል ማሳደግና በባንኩ ዘርፍ ተወዳዳሪ ለመኾን እንደሚሠራ በሪፖርቱ ቀርቧል።
ዘጋቢ፡- አደራው ምንውየለት
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!