የሰላም ጥሪውን ተከትሎ የታየው ለውጥ አበረታች እና ተስፋ ሰጭ መኾኑን የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ አስታወቀ፡፡

30

ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ለወራት የዘለቀውን እና ዘርፈ ብዙ ሰብዓዊ፣ ቁሳዊ እና ማኅበራዊ ጉዳት ያስከተለውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመቋጨት የሚያስችል የሰላም ጥሪ ከቀናት በፊት በክልሉ መንግሥት ተላልፏል፡፡

የሰላም ጥሪውን ተከትሎ አበረታች እና ተስፋ ሰጭ ምላሾች እየተስተዋሉ መኾኑን የክልሉ መንግሥት ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ አስታውቋል፡፡

በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማእረግ የአሥተዳደር ጉዳዮች ዘርፍ አስተባባሪ እና የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ ደሳለኝ ጣሰው “በክልሉ መንግሥት እና ሕዝብ ላይ የተቃጣው ጥቃት ተገቢ ያልነበረ እና ብዙ ዋጋ ያስከፈለ ነበር፤ የኅለውና ስጋቱን በመቀልበስ አንጻራዊ ሰላም ማስፈን ተችሏል” ብለዋል፡፡

የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ለማጽናት እና የሕዝብን የሰላም ጥያቄ ለመመለስ ከቀናት በፊት የክልሉ መንግሥት ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ ጋር በመነጋገር ለታጠቁ ኃይሎች ሁሉ የሰላም ጥሪ ማስተላለፉን ገልጸዋል፡፡

የሰላም ጥሪው የክልሉን መንግሥት ያደገ የሰላም ፍላጎት ማሳያ ነው ያሉት አቶ ደሳለኝ፤ ተጨማሪ ጉዳት እና ውድመት ላለማስተናገድ ከመነጨ ፍላጎት የቀረበ አማራጭ መንገድ መኾኑን ተናግረዋል፡፡

የክልሉ መንግሥት ያቀረበው የሰላም ጥሪ የታጠቁ እና በየትኛውም ጠርዝ ላይ የቆሙ ወገኖችን ሁሉ የሚያካትት ነው ተብሏል፡፡ አሁንም የሰላም ጥሪው የታቀደለትን ዓላማ እንዳያሳካ የሚሹ ግጭት ጠማቂዎች መኖራቸውን ያነሱት አቶ ደሳለኝ፤ ፍላጎታቸውን መመርመር እና ጆሮ መንሳት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ የሰላም ጥሪው የተሳካ እንዲኾንም ወጣቶች፣ ምሁራን፣ በውጭ የሚኖሩ ወገኖች እና የማኅበረሰብ አንቂዎች የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡

የሰላም ጥሪው ከተላለፈበት ጊዜ ጀምሮ ሰላማዊ የትግል አማራጮችን በመምረጥ በርካታ ታጣቂዎች በየአካባቢው በሚገኙ የኮማንድ ፖስት ማዕከላት እየገቡ እንደኾነም አንስተዋል፡፡ ሰላም ድንበርም ኾነ የተለየ ባለቤት የለውም ያሉት አቶ ደሳለ፤ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች የታየውን የሰላም ጭላንጭል እውን በማድረግ የድርሻቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል፡፡

የሰላም ጥሪውን ተቀብለው የሚገቡ ታጣቂዎች የተሃድሶ ሥልጠና እንደሚሰጣቸው የገለጹት ኀላፊው ከተሃድሶ ሥልጠናው ጎን ለጎን በማኅበረሰቡ ዘንድ ቂም፣ በቀል እና ደም መመላለስ እንዳይኖር ማኅበረሰባዊ እርቅ ለመፍጠር የሚያስችል እርቀ ሰላም እንዲኖር መሥራት ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡

በየደረጃው የሚገኘው የመንግሥት የጸጥታ መዋቅርም የሰላም ጥሪውን የተቀበሉ ወገኖችን በመቀበል አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ትዕዛዝ ተላልፏልም ብለዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleማንቸስተር ሲቲ ከክሪስታል ፓላስ ወሳኝ ጨዋታ ያደርጋሉ፡፡
Next articleአንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ በበጀት ዓመቱ 4 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ መሠብሠቡን ገለጸ።