
ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዴ ጋር በጄኔቫ ተወያይተዋል ።
አቶ ደመቀ መኮንን በውይይቱ ላይ እንደገለጹት፤ ከአንድ ሚሊየን በላይ የውጭ ስደተኞች መኖሪያ የሆነችው ኢትዮጵያ የስደተኞችን ሕይወት ማሻሻል እና ምቹ ሁኔታን መፍጠር የሚያስችሉ ስድስት ቃል ኪዳኖችን በመፈፀም ላይ እንደምትገኝ ገልፀዋል።
የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም፣ የግል ዘርፉን ተሳትፎ ማሳደግ፣ ትምህርት፣ ዲጂታል ኮሙኒኬሽንን ተደራሽ ማድረግ ከቃል ኪዳኖቹ መካከል የሚጠቀሱ መሆናቸውንና ባለፉት አራት አመታት ስለነበራቸው አፈፃፀም ገለፃ አድርገውላቸዋል።
ስደተኞች እና ተቀባይ ማኅበረሰብ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል መንግሥት ቃል ኪዳኖቹ ተፈፃሚ እንዲሆኑ በቁርጠኝነት መሥራቱን እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዴ በበኩላቸው የመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን የረጅም ዓመታት አጋርነት አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ አቶ ደመቀ መኮንን በትናንትናው ዕለት ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ጉዳይ ልዩ አማካሪ ሮበርት ፒፐር ጋር ተወያይተዋል።
ሁለቱም ወገኖች ተፈናቃዮችን ለመጠበቅ እና ለመርዳት እና ወደ አካባቢያቸው የሚመለሱበትን ሁኔታ የበለጠ ለማሳደግ መስማማታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!