
አዲስ አበባ: ታኅሳሥ 05/2016 (አሚኮ) ኢትዮ ቴሌኮም ለኅብረተሰቡ ሁለንተናዊ ለውጥ እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ትልቅ ትርጉም ያላቸውን የዲጂታል መፍትሔዎች ለማቅረብ በትኩረት እየሠራ መኾኑን አስታውቋል፡፡ ተቋሙ ከዚህ በፊት ከተለመደው አግልግሎት እጅግ የላቀ የድምጽ እና የምስል ጥራት (Hd calls) ያለው የስልክ ጥሪ ለመቀበል የሚስችል ቮልቲኢ (volte voice over long term evolution) የተሰኘ እና ሌሎች አገልግሎቶችን ዛሬ በይፋ አስጀምሯል፡፡
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬሕይወት ታምሩ የላቀ ተሞክሮዎችን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ዘመኑ ያፈራቸው አግልገሎቶች በዛሬው ዕለት ይፋ መኾናቸውን ተናግረዋል፡፡ እነዚህ አገልግሎቶች የደንበኞችን የቴክኖሎጂ እና የዲጂታል ፍልጎቶች ለማሟላት እንደሚያግዙም ተናግረዋል።
ከአግልግሎቶች አንዱ የቮልቲኢ አገልግሎት ሲኾን ያለምንም የአካባቢ የድምጽ ብክለት ጥራት እና ፍጥነት ያለው የደምጽ ጥሪ ያደርጋል። ዳታ/ኢንርኔት/ ሳያበሩ የድምጽ ወይም የምስል ጥሪዎችን በመቀያየር በተሻለ የባትሪ ቆይታ ጊዜ አገልግሎትን ለመጠቀም የሚያስችል ነው ሲሉም ወይዘሪት ፍሬሕይወት አብራርተዋል፡፡
አገልግሎቱ ደንበኞች ከኔትወርክ ሽፋን ውጭ ሲኾኑ፣ ስልካቸው በሌላ ጥሪ ሲያዝ፣ ሲጠፋ (switch off) ወይም በተለያዩ ምክንያቶች ጥሪ መቀበል በማይችሉበት ጊዜ ደዋዮች በድምጽ የተቀረጸ መልዕክት እንዲያስቀምጡ የሚያስችልም ነው ብለዋል ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ።
ሪች ቢዝነስ የመልዕክት እና የመልቲሚዲያ መልዕክት አግልገሎትም ይፋ ከኾኑት አገልግሎቶች ውስጥ ናቸው፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም ግለሰቦችና ድርጅቶች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸውን እንዲሁም ሥራቸውን የበለጠ ውጤታማ እና ቀልጣፋ ለማድርግ የሚያስችሉ እና ሀገራዊ ፋይዳ የሚያመጡ ሥራዎች እያከናወነ ነው ሲሉም ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ሳሙኤል ኪሮስ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!