
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ሸዋ ዞን ሲያደብር እና ዋዩ ወረዳ በወቅታዊ የሰላም ሁኔታ ላይ ውይይት እየተደረገ ነው፡፡ በውይይቱ በክልሉ መንግሥት የቀረበውን የሰላም ጥሪ በመቀበል ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚገባ ተመላክቷል።
ክልሉ በገጠመው የጸጥታ ችግር አመራሮችን ጨምሮ የሰዎች ሕይዎት የጠፋበት እና ንብረት የወደመበት እንደነበረም የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ መካሻ ዓለማየሁ አስረድተዋል። የጤና፣ የትምህርት እና የተለያዩ አገልግሎቶች ተቋርጠው ቆይተዋል ነው ያሉት። ክስተቱም የክልሉን ሕዝብ ወደኋላ የመለሰ እንደኾነም አሥተዳዳሪው አብራርተዋል።
አሁን ላይ የክልሉ መንግሥት ያስተላለፈውን የሰላም ጥሪ ተጠቅሞ ወደ ሰላም በመመለስ የሕዝቡን ሰላም በዘላቂነት ማረጋገጥ ይገባል ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል። የማዕከላዊ ሸዋ ኮማንድ ፖስት ሠብሣቢ ብርጋዴር ጄኔራል አበባው ሰይድ ክልሉ ካለፈው ጦነት ችግር በቅጡ ሳያገግም ለሌላ ጦርነት መዳረግ አልነበረበትም ብለዋል።
በጦርነት የሚገኝ ትርፍ እንደሌለም የቅርብ ጊዜ ታሪክ ያሳየናል ያሉት ብርጋዴር ጄኔራሉ ይህንን በመረዳት የተከፈተውን የሰላም በር በመጠቀም ወደ አዋጩ ሰላም መግባት እንደሚገባም አሳስበዋል።
ተሳታፊዎቹም በነበረው ችግር በጉስቁልና እና በስጋት ውስጥ እንዳለፉም አስረድተዋል፡፡ የሰላም ጥሪውም በአግባቡ ከተተገበረ ከፊታቸው ተስፋ እንደሚኖር ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
ዘጋቢ፡- ለዓለም ለይኩን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!