
ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የፈጣሪ ምልክት የኾነውን ሰላም መጠበቅ የሁሉም ድርሻ ሊኾን እንደሚገባ የሃይማኖት አባቶች መክረዋል፡፡ የባሕር ዳር ርዕሰ ከተማ ወረዳ ቤተ ክህነት ጽሕፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ እና የሃይማኖት ተቋማት ሰብሳቢ መልዓከ ሰላም ለዓለም ጌታሁን እንዳሉት ሰላም የቤተክርስቲያኗ አስተምህሮ የአፍ መፍቻ ቋንቋ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ስለ ሰላም ሁሌም በዝማሬዋ፣ በቅዳሴዋ እና በማሕሌቷ ለሰው ልጆች ሁሉ ታስተምራለች ብለዋል፡፡
ከኅዳር 15/2016 ዓ.ም እስከ ታህሳስ 27/2016 ዓ.ም የሚቆይ የጸሎት ጊዜ በቅዱስ ሲኖዶስ ታውጆ ስለ ሰላም እየጸለየች መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ ሰላምን በመዘመር ብቻ መረጋጋት አይቻልም፤ ይልቁንም ዝማሬው ከልብ የመነጨ፣ ኹሉን አሳታፊ እና ተግባራዊ ሊኾን ይገባል ብለዋል፡፡
የሁሉም ነገር መሰረት የሆነውን ሰላምን ለማስፈን ኹሉም የድርሻውን ወስዶ ሊሠራ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ በተለይም ኀላፊነት ላይ የተቀመጡ በየደረጃው እና በተለያዩ ተቋማት ያሉ ኀላፊዎች ትልቁን ድርሻ ሊወስዱ ይገባል ብለዋል፡፡ የችግሩን ምንጭ መለየት እና ዘላቂ መፍትሔ ማስቀመጥ እንዳለባቸውም አንስተዋል፡፡ ከዚህም ባለፈ ታዋቂ ሰዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና ምሁራን ለሀገራቸው እንዲሠሩ ጠይቀዋል፡፡ ማኅበረሰቡም ስለ ሰላም በጸሎት ጭምር ማሰብ እንዳለበትም መክረዋል፡፡
የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የዳዕዋ እና የትምህርት ዘርፍ ኀላፊ ሼህ ሙሐመድ ኢብራሂም እንዳሉት የሰላም መነሻ አሏህ በመኾኑ ጸሎት ማድረግ ይገባል፡፡
የሰላም አስፈላጊነት በተደጋጋሚ በቁርዓን መጠቀሱን ገልጸዋል፡፡
ሼህ ሙሐመድ በክልሉ በተከሰተው የሰላም እጦት መልካም ነገሮች ታጥተዋል፤ ችግሮችም አጋጥመዋል፡፡ የእምነቱ አባቶች ከምዕመናን ጋር ተገናኝተው ጸሎት ለማድርስ እና ከፈጣሪያቸው ጋር ለመታረቅ ችግር ኾኖ ቆይቷል፡፡ ከሃይማኖታዊ ክዋኔዎች ባለፈ ዓለማዊ ተግባራትን ለመከናወን ጭምር ፈታኝ እንደነበር ነው ሼህ ሙሐመድ ያነሱት፡፡
በሚከሰቱ ግጭቶች ተጎጅው ራሱ የክልሉ ሕዝብ መኾኑን በመረዳት ችግሮችን በሰላም መፍታትን አማራጭ አድርጎ መውሰድ ይገባል ብለዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ምዕመናን ፈጣሪያቸውን በጸሎት ከመለመን ባለፈ የራሳቸውን አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ ይገባል ብለዋል፡፡ ከጭካኔ በመውጣት የመተዛዘን፣ የመከባበር፣ የመደማመጥ፣ የመረዳዳት ጊዜ እንዲኾንም ተመኝተዋል፡፡
ሁሉም ለሰላም ይቁም፤ ሰላም ባለበት ኹሉ ሁሉም ነገር አለ ብለዋል የሃይማኖት አባቶቹ፡፡
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!