“ሰላምን መርጠው የተመለሱ ሁሉ የተሃድሶ ሥልጠና ወስደው ሕዝባቸውን በሚክስ ሥራ ላይ ለመሰማራት ያስችላቸዋል” አቶ ይርጋ ሲሳይ

57

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የ2016 ዓ.ም የአምስት ወራት የሥራ እንቅስቃሴውን በባሕር ዳር ከተማ ገምግሟል። በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ የአማራ ክልልን የሰላም ችግር በዘላቂነት በመፍታት ለሁሉም የሚበጅ የፖለቲካ ባሕል ለመገንባት እየተሠራ ነው ብለዋል።

የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ለሕዝብ የሚሠሩ ጠንካራ አመራሮችን ለመገንባት እና ለማደራጀት ጠንክሮ እየሠራ እንደሚገኝም ገልጸዋል። አመራር የማደራጀት ሥራው ከክልል እስከ ወረዳ ድረስ በውጤታማነት ስለመጠናቀቁም ጠቁመዋል።

ኀላፊው የሚናበብ፣ የሚደጋገፍ፣ የተሻለ ሥነ ምግባር ያለው እና ሙሉ አቅሙን እንዲሁም ጊዜውን ሕዝብን ለማገልገል የሚያውል አመራር እንዲፈጠርም የማያቋርጥ ድጋፍ እና ክትትል እየተደረገ ነው ብለዋል። ይህም ጠንካራ ሕዝብ እና ጠንካራ ሀገር ለመገንባት እድል የሚሰጥ ነው ብለዋል።

አቶ ይርጋ በክልሉ ያለውን አሁናዊ የሰላም ሁኔታም አንስተው ማብራሪያ ሰጥተዋል። አሁን ላይ ክልሉን ሰላም እያሳጡ ያሉ አካላት እየፈጸሙ ያሉት ድርጊት በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ክልሉን ዝቅ የሚያደርግ ሕዝቡንም ወደኋላ የሚያስቀር ነው ብለዋል።

የጸጥታ መዋቅሩ በክልሉ በፈጠረው ምቹ ሁኔታ ፓርቲው መደበኛ እና ወቅታዊ ሥራዎችን የማከናወን እና የአመለካከት ዝንፈቶችን የማረም ሥራ ሲያከናውን መቆየቱንም ገልጸዋል።

አቶ ይርጋ የክልሉ አመራሮች እና ሰላም ወዳዱ ሕዝብ ለሰላም መስፈን በቁርጠኝነት በመሥራታቸው ክልሉ አንጻራዊ ሰላም እያገኘ ስለመኾኑ አመላክተዋል። የአማራ ክልል ሕዝብ የጠማው ሰላም እና ልማት ነው፤ የገጠመውን ችግር በመፍታት ሕዝቡን በልማት ለመካስ ሌት ተቀን እየተሠራ ነው ብለዋል። በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች የልማት ሥራዎች በፍጥነት እንዲጀመሩ እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል።

አማራ ክልል ወደ ለየለት ሁከት እንዲገባ የሀሰት ፕሮፖጋንዳ እና መራዥ ውሸት ሲዘሩ የነበሩ አካላት ውሎ አድሮም ቢኾን ሀሳባቸው ገዥ አጥቷል ብለዋል። “አመዛዛኙ የአማራ ሕዝብ እውነት እና ሀሰትን፣ ጠቃሚና ጎጅን በትክክል መዝኖ ተረድቷል” ሲሉም ገልጸዋል።

ሕዝቡ ሰላሙን የሚነጥቁትን፣ ለዘመናት የያዛቸው ጥያቄዎቹ እንዳይፈቱ የሚያደናግሩትን፣ ልማቱን የሚያቋርጡበትን፣ ልጆቹን ከትምህርት ገበታ አስቀርተው የሥነ ልቦና ተጠቂ የሚያደርጉበትን፣ እንዲኹም በነጻ አውጭነት ሰበብ መንገድ እየዘጉ ሃብት እና ንብረቱን ለመዝረፍ የሚቋምጡትን በውል ለይቶ ተገንዝቧል ብለዋል። ተገንዝቦም በየአካባቢው እየተወያየ እነዚህን አካላት በቃችሁ ለማለት ችሏል ነው ያሉት።

በቴዎድሮስ ስም እየማለ ሀገር የሚበትን፣ በእምየ ምኒልክ እያለ የምኒልክን ታሪክ ዝቅ በሚያደርግ ብልሹ ሥራ የሚዘፈቅ፣ በበላይ ዘለቀ አምላክ እያለ የበላይን ጀግንነት የማይመጥን የመንደር አሉባልታ ውስጥ የሚርመጠመጥ ኹሉ ውሎ አድሮም ቢኾን ግብሩ እና ተግባሩ በሕዝብ ተገልጧል ነው ያሉት።

የሕግ ማስከበር ሥራውን ከሕዝብ ጋር ተቀናጅቶ ማከናወን በመቻሉም ውጤት ተመዝግቧል ነው ያሉት። አሁንም ቢኾን የሰላም ጥሪ ተደርጓል፤ በጥሪው የመጀመሪያ ቀን ብቻ በርካታ ወጣቶች ከአልባሌ እንቅስቃሴ ወጥተው ሰላምን መርጠዋል ብለዋል።

እነዚህ ወጣቶች የእኛው ናቸው፣ ሰላምን መርጠው የተመለሱ ኹሉ የተሃድሶ ሥልጠና ወስደው ሕዝባቸውን በሚክስ ሥራ ላይ ለመሰማራት ያስችላቸዋል” ሲሉም አቶ ይርጋ አረጋግጠዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የኢትዮጵያ አየር ኃይል ጥንካሬ ከኢትዮጵያ ህልውና ጋር የሚቆራኝ ነው” ጀኔራል አበባው ታደሰ
Next articleትኩረት ያገኙ የስምንተኛ ሳምንት መርኃ ግብሮች ዛሬ ይካሄዳሉ።