“የኢትዮጵያ አየር ኃይል ጥንካሬ ከኢትዮጵያ ህልውና ጋር የሚቆራኝ ነው” ጀኔራል አበባው ታደሰ

53

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀኔራል አበባው ታደሰ ይህንን ያሉት 88ተኛ ዓመት የኢትዮጵያ አየር ኃይል ተቋማዊ አቅም እና ሒደት ላይ መሠረት ያደረገ የፓናል ውይይት በቢሾፍቱ ሲካሔድ ነው።

የኢትዮጵያ ቀጣይነት እንዲረጋገጥ የኢትዮጵያ አየር ኃይል መቀጠል እና መጠናከር አለበት ብለዋል። የሀገሪቱን አንድነት በማረጋገጥ ለምድር ኃይሉ አቅም በመኾን እና በማገዝም ከፍተኛ ሚና አለው ብለዋል።

እኛ ማንም እንዲያከብረን አንፈልግም እንዲነቅፈንም አንፈልግም ራሳችን በራሳችን ሠራዊት የምንተማመን በመስዋዕትነት ከዚህ የደረስን ነን ብለዋል።

አየር ኃይሉ የነበረውን ተቋማዊ ጉዞ ያቀረቡት የኢፌዴሪ አየር ኃይል አዛዥ ሌተናል ጀኔራል ይልማ መርዳሳ አየር ኃይሉ በተቋም ደረጃ ስያሜ ያገኘበት በ1928 መኾኑን ገልጸዋል፡፡
በዘመኑ አየር ኃይሉ ውጊያን በትራንስፖርት ሲያግዝ እንደነበርም አውስተው በኋላም የተለያዩ የውጊያ አቅሞችን የመገንበት ሥራዎች ሲሠራ ነበር ብለዋል።

ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማሪያም ጋር በመመካከር ሜጄር ጀኔራል ፈንታ በላይ አሁን ያለውን ግቢ ተቋማዊ ቅርፅ እና ጥንካሬ እንዲኖረው ያደረጉ መኮንን ናቸው ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል በከፍተኛው ደረጃ የውጊያ የተቋም እና የአሸናፊነት ስሜት የተጎናጸፈበት ጊዜ እንደነበር አንስተዋል።

በኢህአዴግ ዘመን የነበረው የአየር ኃይል ታሪክ ደግሞ በከፍተኛ ሁኔታ ኃይሉ በሠራዊትም በተዋጊ ጀቶችም የተበተነበት ትጥቅም አቅሙም የሌለው ነበር ብለዋል። ከ5 ዓመታት በፊት አየር ኃይሉ ለነበረው ግዳጅ የአየር መንገድ ተከራይቶ ያጓጉዝ ነበር ብለዋል። በኢህአዴግ ዘመን በአየር ኃይሉ ከፍተኛ ጣልቃ ገብነት ነበር እሱ አየር ኃይሉን ጎድቶት ቆይቷል። ፖሊሲም አልነበረው ብለዋል።

በፀረ አልሸባብ ዘመቻም አየር ኃይሉ የተወሰነ አቅም መፍጠር ችሎ የነበረ መኾኑን በመጥቀስ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ደግሞ በከፍተኛ ሁኔታ መነቃቃት አሳይቶ እንደነበር ጠቅሰዋል።
በብልጽግና ዘመነ መንግሥት ወቅትም አየር ኃይሉ በመንግሥት ደረጃ አቋም ተወስዶ እንዲቀየር መሠራቱን እና ለውጥ መምጣቱን ሌቴናል ጀኔራል ይልማ ገልጸዋል፡፡

የፖሊሲ ለውጡም በውጊያ፣ በመሠረተ ልማት፣ በሰው ኃይል እና በጽንሰ ሃሳብ የተሟላ ሥራ በመሥራት አሁን ከፍተኛ አቅምን መፍጠር ችለናል፤ በ2022 ዓ.ም ከአፍሪካ ቀዳሚ አየር ኃይል ለመኾን እየሠራን ነው ብለዋል።

ዘጋቢ፡- አንዷለም መናን

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአማራ ክልል ከ60 በላይ ለሚኾኑ የመንገድ ፕሮጄክቶች ከ90 ቢሊዮን ብር በላይ ተመድቧል።
Next article“ሰላምን መርጠው የተመለሱ ሁሉ የተሃድሶ ሥልጠና ወስደው ሕዝባቸውን በሚክስ ሥራ ላይ ለመሰማራት ያስችላቸዋል” አቶ ይርጋ ሲሳይ