በአማራ ክልል ከ60 በላይ ለሚኾኑ የመንገድ ፕሮጄክቶች ከ90 ቢሊዮን ብር በላይ ተመድቧል።

37

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ርእሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደ በተገኙበት በአማራ ክልል እየተገነቡ የሚገኙ የመሠረተ ልማት ሥራዎች ተገምግመዋል።
የርእሰ መሥተዳድሩ የመሠረተ ልማት አማካሪ ደሴ አሰሜ በአማራ ክልል በፌዴራል መንግሥት የሚገነቡ የመሠረተ ልማት ፕሮጄክቶች መኖራቸውን ገልጸዋል።
በተለያዩ ምክንያቶች ተጀምረው የቆሙ የመሠረተ ልማት ፕሮጄክቶች መኖራቸውንም ተናግረዋል። በተቋራጮች አቅም ማነስ፣ በፀጥታ እና በሌሎች ምክንያቶች የቆሙትን ማስጀመር ይገባል ነው ያሉት።

በእቅድ ያሉ እና ወደ ሥራ ያልገቡ ፕሮጄክቶችን ለማስጀመር እና የተጀመሩትን ለማስፈፀም የሚያስችል ውይይት መደረጉንም ነው የተናገሩት። ውይይቱ የተጓተቱ ፕሮጀክቶችን ለማስጨረስ እና የተቋረጡ ፕሮጄክቶችን ለማስጀመር እንደሚያስችልም ተናግረዋል።

በአማራ ክልል የመሠረተ ልማት ግንባታ ኢፍትሐዊነት አለ የሚል ጥያቄ መኖሩን ያነሱት አማካሪው የመሠረተ ልማት ጥያቄዎችን እና ችግሮችን ለመፍታት በርካታ እቅዶች መኖራቸውንም አመላክተዋል። በወሰን ማስከበር ችግር፣ በጸጥታ ሁኔታ እና በሌሎች ችግሮች ፕሮጄክቶች እንደሚጓተቱ እና እንደሚቋረጡም ገልጸዋል።

በፌዴራል መንግሥት የካሳ ክፍያ መዘግየት እና በተቋራጮች ችግር መኖርም የሚዘገዩ ፕሮጄክቶች መኖራቸውን ተናግረዋል። ፕሮጄክቶች በሚፈለገው ጊዜ ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት እንዲኾኑ ለማድረግ ውይይት መደረጉንም አንስተዋል።

ሰላም ለመሠረተ ልማት ወሳኝ ነው ያሉት አማካሪው ልማት ያለ ሰላም ሊኾን አይችልም፣ ልማትም ከሌለ ለሰላም መናጋት ምክንያት ይኾናል ነው ያሉት። የሰላም መኖር ፕሮጄክቶችን ለመተግበር ጠቀሜታው የጎላ መኾኑንም ገልጸዋል። የተሻለ ልማት ለመሥራት እና ሕዝብን ተጠቃሚ ለማድረግ ሰላም አስፈላጊ በመኾኑ ለሰላም እየተደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል ብለዋል።

በክልሉ ከ60 በላይ የመንገድ ፕሮጄክቶች መኖራቸውን ያነሱት አማካሪው ለመንገድ ፕሮጄክቶች ከ90 ቢሊዮን ብር በላይ መመደቡን ገልጸዋል። ፕሮጄክቶቹ ሲሠሩ የሥራ እድል ከመፍጠር ጀምሮ ለኅብረተሰቡ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች እንደሚኖራቸውም አንስተዋል።

ፕሮጄክቶችን ለመገንባት ሰላም መኖር እንደሚገባውም ገልጸዋል። ሁሉም ለሰላም የድርሻውን መወጣት እንደሚገባውም አሳስበዋል። ለሰላም የትኛውም አካል ድርሻ እንዳለው አመላክተዋል።

በግምገማው የመሠረተ ልማት ጥያቄዎችን በአግባቡ መፍታት እንደሚገባ ተመላክቷል። የክልሉን ሕዝብ ተጠቃሚ የሚያደርግ የመሠረተ ልማት ሥራዎችን የመሥራት ውስንነቶች መኖራቸውም ተገልጿል። የመሠረተ ልማት ችግሮችን መፍታት እና ሕዝብን ተጠቃሚ ማድረግ ይገባልም ነው የተባለው። ሰላም ባለባቸው አካባቢዎች ገብቶ መሥራት እንደሚገባም ተመላክቷል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleለታክስ ገቢ መቀነስ ምክንያቶችን በመለየት መፍትሔዎቹ ላይ በጥልቀት መነጋገር እንደሚገባ የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሤ አሳሰቡ።
Next article“የኢትዮጵያ አየር ኃይል ጥንካሬ ከኢትዮጵያ ህልውና ጋር የሚቆራኝ ነው” ጀኔራል አበባው ታደሰ