
አዲስ አበባ: ታኅሳሥ 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በ2011 በጀት ዓመት 9 ነጥብ 72 በመቶ የነበረው የታክስ ገቢ በ2015 በጀት ዓመት ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት ጥምርታ አንጻር ሲታይ ወደ 7 ነጥብ 02 በመቶ ዝቅ ማለቱን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ያለደረሰኝ ግብይት፣ የሐሰተኛና ከዋጋ በታች የሚሰጡ ደረሰኞች ሥርጭት እና የኮንትሮባድ ንግድ ሰንሰለት ውስብስብ መኾን፣ የሕገወጥ ንግድ እና የህቡዕ ኢኮኖሚ መስፋፋት ለታክስ አሰባሰብ ሥርዓቱ ዋነኛ ማነቆዎች መኾናቸውን የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሤ ተናገሩ።
በየዓመቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚሰበሰበው የታክስ እና የቀረጥ ገቢ እየጨመረ የመጣ ቢኾንም የዓለም አቀፍ የታክስ አሰባሰብ ውጤታማነት መለኪያ አንዱ በኾነው የታክስ ገቢ ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት ጥምርታ አንጻር ሲታይ የአፈጻጸም ውጤታችን በተቃራኒው መኾኑም ተጠቁሟል፡፡
እንደማሳያም በ2011 በጀት ዓመት 9 ነጥብ 72 በመቶ የነበረው በ2015 በጀት ዓመት የታክስ ገቢ ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት ጥምርታ አንጻር ሲታይ ወደ 7 ነጥብ 02 በመቶ ዝቅ ማለቱን ጠቅሰዋል፡፡ ለመቀነሱ ምክንያቶች ባይታወቁም የችግሮቹን ምንጮች ለይቶ በማውጣት መፍትሔዎቹ ላይ በጥልቀት መነጋገር እንደሚገባም ሚኒስትሯ አሳስበዋል፡፡
የወጪ እና ገቢ ኮንትሮባንድ ጉዳይም በየጊዜው መልኩን እየቀያየረ የንግድ ሥርዓቱን በማዛባት የታክስ አሰባሰብ ሥርዓታችንን እየተፈታተነው ይገኛል ብለዋል ሚኒስትሯ፡፡ ስለኾነም የቁጥጥር ሥርዓታችንን መለስ ብለን መፈተሽ እና ማጠናከር ይጠበቅብናል ነው ያሉት፡፡
ሕገወጦችን ወደ ሕጋዊ ሥርዓቱ እንዲገቡ ማድረግ፣ ካልኾነም የሕግ ማስከበር ሥርዓታችንን ተጠቅመን አስፈላጊውን ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድ ቁርጠኛ መኾን ይኖርብናል ነው ያሉት፡፡ እንደሀገር ያለንን የአሠራር ሥርዓት በቴክኖሎጂ በማስደገፍ ለሌብነት እና ለማጭበርበር ያልተመቸ ማድረግ ያስፈልጋል ነው ያሉት ሚኒስትሯ፡፡
ሀገራችን ያላትን የልማት ፍላጎት ለማሟላት ገቢ ሰብሳቢ ተቋማት እና ባለድርሻ አካላት ከማኅበረሰቡ ጋር በመቀናጀት የታክስ ሕግ ተገዥነትን በማስፈን ገቢ በብቃት መሠብሰብ ይገባል ብለዋል፡፡
በሀገር አቀፍ ደረጃ የታክስ ሥርዓቱ ወጥ እና የተጣጣመ መኾን ይኖርበታል ያሉት ሚኒስትሯ የክልል እና የከተማ አሥተዳደር ገቢ ሰብሳቢ ተቋማት ከፌዴራል የሚወጡ የታክስ ሕጎችን ከራሳችው ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማጣጣም ተግባራዊ ማድረግ እንደሚኖርባቸውም አሳስበዋል፡፡ ከዛሬ ጀምሮ ለሁለት ቀናት በሚኖረው የምክክር መድርክ ላይ በርካታ ጉዳዮች ውይይት እንደሚደረግባቸው በመድረኩ ተገልጿል፡፡
ዘጋቢ፡- ድልነሳ መንግስቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!