
ባሕር ዳር፡ የካቲት 12/2012 ዓ.ም (አብመድ) ባሕር ዳርን የዘንባባ ካባ ያጎናጸፏት አቶ ዋሴ አካሉ የሁለት ክፍል ቤቶችን ቁልፍ ተረክበዋል፡፡
ባሕር ዳር ከተማን ስናሰታውስ ቀድሞ በአዕምሯችን ድቅን የሚለው ውበቷ ነው፡፡ ሥለ ባሕር ዳር ከተማ ውበት ሲወሳ ደግሞ በከተማዋ መንገዶች ግራና ቀኝ በሥርዓት ተሰድረው ልዩ ገጽታ ያጎናጸፏት ዘንባባዎቿን ማስታወስ ግድ ይላል፡፡ ዘንባባዎቿ ሁሌም በናፍቆት እንድትታይ ያደርጓታል፡፡ ጣናን ከትረሷ፣ አባይን ከወገቧ አድርጋ ብታሸበርቅም ባሕር ዳር ዘንባባዎቿን ካላጎፈረች ውበቷ ምሉዕ አይሆንም፡፡
ከዚህ ሁሉ ውበት በስተጀርባ ደግሞ አንድ አዛውንት አሉ፤ የባሕር ዳር ነዋሪው አቶ ዋሴ አካሉ፡፡ የ95 ዓመቱ የዕድሜ ባለጸጋ የባሕር ዳር ከተማ ውበት ባለውለታ ናቸው፤ በልዩ መገለጫ ዘንባባዎቿ ከተማዋን አረንጓዴ ካባ አጎናጽፈው ከማስዋብ ባለፈ ለነዋሪዎቿ የእስትንፋስን ምንጭም ሆነዋልና፡፡ አቶ ዋሴ ጡረታ እስከወጡበት ጊዜ ድረስ በመንግሥት ሥራ አገልግለዋል፡፡ ለባሕር ዳር የዘንባባ መጎናጸፊያ የደረቡላትም በከተማው የጽዳት እና ውበት ሠራተኛ በነበሩበት ወቅት ነው፡፡
ጊዜውም ደግሞ ጥቅምት 01/1949 ዓ.ም ነበር፤ የዛሬ 63 ዓመት፡፡ በወቅቱ የከተማ አስተዳደሩ የዘንባባ ችግኞችን ከአስመራ ሲያስመጣ አቶ ዋሴ 50 ሠራተኞችን በማስተባበር፣ አብረው በመትከል እና በመንከባከብ ከፍተኛውን ድርሻ ተወጥተዋል፡፡
ከከተማዋ ልዩ ውበት በስተጀርባ ያሉት አዛውንቱ አቶ ዋሴ በአሁኑ ጊዜ እርጅና ተጫጭኗቸው አቅም አንሷቸዋል፡፡ በጡረታ ከሚያገኙት ገቢ ሌላ የገቢ ምንጭ ስለሌላቸውም ለችግር መጋለጣቸውን ሰምተናል፡፡
የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም (አብቁተ) የባለውለታውን ችግር በመረዳትና የገቢ ማስገኛ እንዲሆናቸው በማሰብ ሁለት ክፍል ቤቶችን በራሳቸው ቦታ ላይ አሠርቶ ዛሬ የካቲት 12/2012 ዓ.ም አስረክቧቸዋል፡፡ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ መኮንን የለውምወሰን ተቋሙ ካሉበት ማኅበራዊ ኃላፊነቶች መካከል ለክልሉም ሆነ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ አስተዋጽዖ አበርክተው አስታዋሽ ያላገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን መርዳት እና እውቅና መስጠት አንዱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ትልቅ ሥራ የሠሩት አቶ ዋሴ አስታዋሽ ማጣታቸው ተገቢነት የሌለው እና ልብ የሚሰብር መሆኑንም አቶ መኮንን ተናግረዋል፡፡ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ዛሬ ቁልፉን አስረክበዋቸዋል፡፡ ድጋፉ በቂ ባይሆንም ሌሎች ተቋማት መሰል ተግባራትን እንዲያከናወኑ እንደሚያነሳሳም ነው አቶ መኮንን የተናገሩት፡፡
እንደ አቶ ዋሴ ላሉ ታላላቅ ሰዎች ላበረከቱት አስተዋጽዖ የሚመጥን ክብር የመስጠት ኃላፊነት ከሌሎች ተቋማት የሚጠበቅ በመሆኑ የበኩላቸውን እንዲወጡም ዋና ሥራ አስፈጻሚው አስተያዬት ሰጥተዋል፡፡ ለአቶ ዋሴ የሚደረገውን ድጋፍ ከማጠናከር ባለፈ ሌሎች ለክልሉና ለሀገር አስተዋጽዖ ያላቸውን ሰዎች በማፈላለግ አብቁተ የመደገፍ ተግባሩን ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል፡፡
በሌላ በኩል የባሕር ዳር ከተማን ውበት በመጠበቅ፣ አባይ እና ጣናም ቆሻሻ እየተጣለባቸው በመሆኑ በመንከባከብ የአቶ ዋሴን ዘመን ተሻጋሪ በጎ ተግባር ማስቀጠል እንደሚገባ ጎረቤቶቻቸው አስተያዬት ሰጥተዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ