
ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሰላም ስትኖር ደስታ ትቀርባለች፣ ሰላም ስትኖር ፍቅር ከፍ ትላለች፣ ሰላም ስትኖር አንድነት ትጠነክራለች፣ ሰላም ስትኖር ምድር ትረጋለች።
ሰላም ስትኖር ከተሞች ይገነባሉ፣ ጎዳናዎች ያምራሉ፣ አርሶ አደሮች በሰፊው ያርሳሉ፣ በሰፊው ያፍሳሉ፣ ሀገር ይመግባሉ፣ ሰላም ሲኖር አበው ጥበብ ያስተምራሉ፣ ትውልድ ያንፃሉ፣ ዕውቀትን እና ታሪክን ይነግራሉ። ልጆች ያድጋሉ፣ አድገው ለቁም ነገር ይበቃሉ፣ የፀናች ሀገር ይረከባሉ፣ ሀገርም ይጠብቃሉ።
ሰላም ስትኖር ኢንዱስትሪዎች ያብባሉ፣ ወጣቶች ሥራ ይይዛሉ። ራሳቸውን ጠቅመው ሀገር ከፍ ከፍ ያደርጋሉ። ሰላም በጠፋች ጊዜ ግን ወጣቶች ያለ እድሜያቸው ይቀጫሉ፣ ሕጻናት በለጋ እድሜያቸው ያልፋሉ። አረጋውያን ጧሪ እና ቀባሪዎቻቸውን አጥተው ብቻቸውን ይቀራሉ።
“ከሰው ሁሉ ጋር ሰላምን ተከተሉ። ትቀደሱም ዘንድ ፈልጉ” እንደተባለ ሰላምን የተከተለ፣ ሰላምን የፈለገ ከፍ ከፍ ይላል። ሰላምን የተከተለ ይቀደሳል። በሰላም ወጥቶ በሰላም ይገባል። ከልጆቹ ፍሬን ያያል፣ ከሥራው ውጤትን ያገኛል። ሰላም የሚከታተሏት፣ ሰላም የሚፈልጓት፣ ሰላም የሚያርፉባት፣ ሰላም የሚረጋጉባት፣ ሰላም ደስ የሚሰኙባት፣ ሰላም የሚያተርፉባት፣ ሰላም የሚጽናኑባት፣ ሰላም ከመከራ እና ከመቅሰፍት የሚተርፉባት ናትና።
ሰላም ከስጦታዎች ሁሉ የበለጠች ስጦታ ናት። ሰላም በሕይዎት ስንኖር ልናጣቸው ከማይገቡ ጉዳዮች መካከል ቀዳሚው ነው። ሰላም መወደድ እና መፋቀር ነውና። ሰላም የሕይዎት ማጣፈጫ ቅመም ናት። ቅመሙ በጠፋ ጊዜ ሕይዎት ትመራለች። ሕይዎት ትጎመዝዛለች፣ መልካም ትዝታና ታሪክ ሳይኖራት ታልፈለች። ሰላም በሌለ ጊዜ ቀናት ይከብዳሉ፣ ወራት ይጨንቃሉ።
በአማራ ክልል ለወራት በዘለቀው የሰላም እጦት ብዙዎች ሕይዎታቸው አልፏል፣ ቆስለዋል፣ ደምተዋል። መንገዶች ተዘጋግተው ብዙዎች በችግር ውስጥ አልፈዋል። በችግር ውስጥ እየለፉ ያሉም አሉ።
ተቋማት ወድመዋል፤ ተዘርፈዋል። ብዙዎችን የሚመግቡ ኢንዱስትሪዎች ተዘግተዋል። ሠራተኞቻቸውን በትነዋል። እነርሱም ለኪሣራ ተጋልጠዋል። እናቶች መንገድ ተዘግቶባቸው በወሊድ ምክንያት በጣር ተጨንቀው አልፈዋል።
በአማራ ክልል በተፈጠረው የሰላም እጦት ውድመት ከደረሰባቸው ተቋማት መካከል ጣና ፍሎራ የአበባ ምርት አንደኛው ነው። ሚሊዮን ብሮችን ለሀገር የሚያስገባው፤ ሺህዎችን የሥራ እድል ባለቤት አድርጎ የሚመግበው በደረሰበት ጥቃት ወድሟል። በርካታ ሠራተኞቹንም በትኗል። የቀሩ ሠራተኞችም ዛሬ ወይስ ነገ እንቀነስ ይኾን በሚል ስጋት ውስጥ ነበሩ። የሰላም መደፍረሱ ከቀጠለ ነገስ ምን እንኾን ይኾን በሚል ጭንቀት ውስጥ ነበሩ።
ከሰሞኑ በአማራ ክልል በመንግሥት የተጠራው የሰላም ጥሪ ደግሞ ስጋታቸውን ወደ ተስፋ ቀይሮላቸዋል። ሰላም ከፀና ድርጅታቸው ወደ ነበረ አቋሙ ይመለሳል። እነርሱም ሳይቀነሱ ይሠራሉ። የተቀነሱትም ተመልሰው ይመጣሉና።
በስልክ ያነጋገርናቸው በጣና ፍሎራ የአበባ ምርት የመስኖ ተቆጣጣሪ መኳንንት ወርቁ “ድርጅታችን በተፈጠረው የሰላም እጦት ከፍተኛ ውድመት ደርሶበታል፤ የደረሰው ጉዳትም መልሶ ለማስጀመር ከፍተኛ ሥራ ይፈልጋል” ነው ያሉት። በተፈጠረው ያልታሰበ ችግር ትዳር የሚመሩ፤ ልጆች የሚያሳድጉ ሠራተኞች ከሥራ ውጭ ኾነው የሰው እጅ እንዲያዩ ተገድደዋልም ይላሉ።
የሰላም አለመኖር ተስፋ አይሰጥም፤ ትርፉ ከነገ ዛሬ ምን ይገጥመን እያሉ በስጋት መኖር ነው። ጣና ፍሎራ ወደ ነበረበት ለመመለስ አስቀድሞ ሰላም ከዚያ በኋላ ደግሞ በርካታ ሥራዎች እና ሃብቶች ያስፈልጉታል ነው የሚሉት። ለወራት በችግር ውስጥ የቆዬው የአበባ ምርቱ ሰላም ከሌለ ነገው አደጋ ነው ብለውናል።
ሰላም ከሌለ ውሎ መግባት፣ ሠርቶ መብላት፣ የእለት ጉርስ ማግኘት ከባድ ነው፣ ሁሉም ለሰላም መዘመር አለበት፣ ችግሮችን በሰላም መፍታት ተመራጭ ነው፣ ሰላም ከሌለ ሁሉም ነገር ይወሳሰባል፣ ሁሉም ነገር ይከብዳል ነው የሚሉት።
ከሰላም በላይ ምንም ነገር የለም፤ ሰላም ሳይኖር ብዙ ነገር ሲወድም አይተናል፣ ሰላም ባለመኖሩ ድርጅታችን ወደነበረበት ሳይመለስ ቆይቷል፣ ሰላም ሲኖር የተዘጉት ይከፈታሉ፤ የወደሙት ይጠገናሉ ይላሉ። ሁሉም ሰው ለሰላም ዝግጁ መኾን አለበት። ጥያቄዎችን በሰላም መጠየቅ፣ በሰላምም መፍታት ይገባል፤ የሰላም እጦት ለብዙ ቀውስ ዳርጎናልና ነው ያሉት።
የሰላም እጦት በመኖሩ ድርጅቱን እንጀራቸው አድርገው የነበሩ ሁሉ ተበትነው ለችግር ተጋልጠዋል፣ ሰላም ሲኖር ግን ይህ ሁሉ ይለወጣል ነው የሚሉት። ሰላም ከሌለ ግን የበለጠ ቀውስ ውስጥ እንገባለን፤ ወደ ተወሳሰበ ቀውስ ውስጥ ላለመግባት ሰላምን ልናስቀድም ይገባል ይላሉ።
ሰላም ከሌለ ሕይዎትን ለመምራት እና ለመኖር አዳጋች መኾኑንም ያነሳሉ። ሰላም የሚጀመረው ከቤተሰብ ነው፣ ከቤተሰብ የተጀመረ ሰላም ወደ ሀገር ከፍ ይላል ነው የሚሉት። የአማራ ክልል መንግሥት ያቀረበውን ሰላም በመስማታቸው ስጋታቸው ወደ ተስፋ መቀየሩንም ነግረውናል።
በጣና ፍሎራ የአበባ ምርት የጄኔሬተር ኦፕሬተር ካሳሁን ዓለማየሁ የሰላም አለመኖር ብዙ ነገር አሳጥቶናል፣ ሠርቶ የሚበላውን ሁሉ ችግረኛ አድርጎታል፣ ለሀገር እና ለሕዝብ የሚጠቅሙ ተቋማትን አውድሟል ነው ያሉት።
ለሰላም ስንሮጥ ብዙ ነገር እናተርፋለን፣ ስለ ሰላም ስንሠራ ከችግር እንወጣለን፣ ውይይት እና ምክክር ማድረግ ያተርፋል፣ ችግርንም ይፈታል ነው የሚሉት። ከሰላም ጥሪው ወዲህ ተስፋ እያዬን ነው፣ ተስፋው እውን ከኾነ ደግሞ እጅግ ደስተኞች ነን፣ በየአካባቢው ውይይት ማድረግ የበለጠ ሰላምን ያመጣል ነው ያሉት።
ባለፉት ጊዜያት ጨላልሞብን ነበር ያሉት የጄኔሬተር ኦፕሬተሩ አሁን ላይ ተስፋ እያዬን ነው፣ ተስፋችን እውን እንዲኾንም ምኞታችን ነው ይላሉ። ይቅርታ ማድረግ ከሕዝብ ጋር አብሮ መሥራት፣ የተሟላ ሰላም እንደሚያመጣም ተናግረዋል።
ጣና ፍሎራ የአበባ ምርት ለአካባቢው ማኅበረሰብ እና ለክልሉ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለውም ገልጸዋል። ሰላም ካለ ጣና ፍሎራ ከወትሮው የተሻለ ኾኖ እንደሚቀጥልም ተስፋ አለኝ ነው ያሉት።
ሰላም ሲኖር ፋብሪካዎች ለወጣቶች ሥራ ይከፍታሉ፣ ወጣቶችም ለሥራ ብቻ ትኩረት ያደርጋሉ ነው የሚሉት። ኅብረተሰቡ በሰላም እጦት ምክንያት ተሳቅቋል፣ ሰላምን ናፍቋል፣ ሠርቶ መብላት፣ ያለ ስጋት መንቀሳቀስን ይፈልጋልም ብለዋል። ግጭት የነበረ ነው የሚሉት ካሳሁን ይቅርታ እያደረጉ ችግርን መፍታት ጥበብ ነው፣ ይቅርታ ሰላም እና ፍቅርን ያመጣል ነው ያሉት።
ያዘኑት እንዲረጋጉ፣ የወደሙት እንዲጠገኑ፣ የተዘጉት እንዲከፈቱ ሰላም የተገባች ናት። ሰላምን ልበሱ፣ ለሰላምም ተመላለሱ። ያን ጊዜ ተስፋዎች ሁሉ እውን ይኾናሉ፣ እቅዶች ሁሉ ይሳካሉ ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!