የመንግሥት ሠራተኞች ከአሉባልታ ወሬ በመራቅ ለሰላሙ ጥሪ ዘብ ሊቆሙ እንደሚገባ የሰቆጣ ከተማ አሥተዳደር የመንግሥት ሠራተኞች ጠየቁ።

40

ሰቆጣ: ታኅሳሥ 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የክልሉን ሰላም ለማረጋጋት እና ፖለቲካዊ ጥያቄዎችን በሕጋዊ መንገድ ለመፍታት የሰላም ጥሪ ካቀረበ ዛሬ ሦስተኛ ቀኑን ይዟል።

ይህንን የሰላም ጥሪ በማስመልከት ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉት የሰቆጣ ከተማ አሥተዳደር የመንግሥት ሠራተኞች የሀገራችንን ሰላም የምናስጠብቀው የተማርን ሰዎች ዕውቀታችንን ለሰላም ግንባታ ስንጠቀምበት ነው ብለዋል።

የሰቆጣ ከተማ አሥተዳደር የመንግሥት ሠራተኛ መስፍን መኮነን ከአሁን በፊት ባሳለፍነው የሰሜኑ ጦርነት ወቅት ቀዳሚ ተጎጅ የነበረው የመንግሥት ሠራተኛው ነበር፣ አኹንም ለሰላም ዘብ ካልቆምን የበለጠ ችግር ያጋጥመናል ነው ያሉት።

የክልሉ መንግሥት ለይቅርታ እና ለሰላም ጥሪ ማቅረቡ ትክክለኛ እርምጃ ነው ያሉት አቶ መስፍን የተዘረጋውን የሰላም እጅ በይቅርታ መቀበል ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ወይዘሮ ሙሉ ወንድሙ ለአሚኮ በሰጡት አስተያየት “የተማረው የኅብረተሰብ ክፍል ለሕዝቡ እውነተኛ እና ትክክለኛ መረጃ በመስጠት ግንዛቤ በመፍጠር ኀላፊነቱን ሊወጣ ይገባል እንጂ፤ በአሉባልታ ወሬ የማኅበረሰቡን ተስፋ ሊበርዘው አይገባም “ነው ያሉት።

የክልሉ መንግሥት የሰላም ጥሪውን ለማወጅ ቢዘገይም መልካም ሥራ መቼም አርፍዶ አያቅም እና ሁላችንም ከሰላም ጎን ልንሰለፍ ይገባል ነው ያሉት ወይዘሮ ሙሉ ወንድሙ።

አቶ ጌታሁን በላይ በበኩላቸው ሀገር ሰላም ካልኾነ ነጋዴው መነገድ፣ የመንግሥት ሠራተኛው ሕዝብን ማገልገል አይችልም። የሰላምን ዋጋ ሁላችንም እናውቀዋለንና ሁሉም ሰው ከሰላም ፈላጊዎች ጎን በመቆም ለሰላም እጁን ይዘርጋ ብለዋል።

“የገበያ ጋጋታ ለሌባ ይመቻል” እንዲሉ እኛ እርስ በእርስ ካልተስማማን የውጭ ኃይሎች እንደ ሶሪያ የአማጽያን መፈንጫ ያደርጉናል “ነው ያሉት አቶ ጌታሁን።
የሰላሙ ጥሪ ፍሬማ እንዲኾን ሁለቱም የድርሻውን እንዲወጣ ሲሉም የመንግሥት ሠራተኞቹ አሳስበዋል።

ዘጋቢ:- ደጀን ታምሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበክልሉ መንግሥት የተላለፈው የሰላም ጥሪ እርስ በእርስ መጠፋፋትን የሚያስቀር እንደኾነ የደባርቅ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።
Next articleየዓድዋ ዜሮዜሮ ፕሮጀክት የደረሰበትን የግንባታ ሂደት የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር አስጎበኘ።