
ደባርቅ: ታኅሳሥ 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል መንግሥት ላለፉት አራት ወራት የተፈጠረውን የሰላም ችግር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያስተላለፈው የሰላም ጥሪ ሦስተኛ ቀኑን አስቆጥሯል፡፡
በተላለፈው የሰላም ጥሪ ላይ አስተያየታቸውን ለአሚኮ የሰጡት የደባርቅ ከተማ እስልምና ጉዳይ ምክር ቤት ሰብሳቢ ዳውድ ቡሽራ ሰላም ለሁሉም አካላት አስፈላጊ ነው ብለዋል።
ያለ ሰላም ቤተክርስቲያንም ኾነ መስጂድ ሄዶ ማምለክ እንዲሁም ለንግድ መንቀሳቀስ አይቻልም ነው ያሉት።
አካባቢው ባለፉት ሦስት ዓመታት በጦርነት ውስጥ ስለነበር ችግር ውስጥ መቆየታቸውን ገልጸው አሁንም በክልሉ በተፈጠረው የሰላም መደፍረስ ከፍተኛ የኑሮ ውድነት ተፈጥሯል ብለዋል። በከተማው የሚታየው የኑሮ ውድነት ሊቀንስ የሚችለው ሰላም ሲኖር ብቻ እንደኾነም አስረድተዋል።
መንግሥት ያስተላለፈው የሰላም ጥሪ ለኅብረተሰቡም፣ መሳሪያ ላነገቡትም ወንድሞች ጠቃሚ ነው ብለዋል። ወንድሞቻችን ሁሉ የሰላም ጥሪውን ተቀብለው ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲቀላቀሉ እና በክልሉ ሰላም እንዲሰፍን አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ እንደሚገባም ነው አስተያየታቸውን የተናገሩት።
ሌላኛው አስተያየት ሰጭ አቶ አስማማው ገብረሥላሴ በተፈጠረው ጦርነት በሁለቱም ወገን የሚሞተው የሰው ልጅ ነው፤ ይህን ለማስቀረት ውይይትን እና መነጋገርን ማስቀደም አስፈላጊ ነው ብለዋል።
በመንግሥት የተደረገው የሰላም ጥሪ ወገኖችን ከሞት ለመታደግ እና ውይይትን ለማስቀደም ስለሚረዳ የሚበረታታ ነው ብለዋል። ለዚህ ደግሞ የሰላም ጥሪው ከልብ ሊኾን እንደሚገባ አቶ አስማማው አሳስበዋል።
ሰላም ከሌለ እድገት የለም፤ የኑሮ ውድነት ከፍ ይላል በዚህ ምክንያት ሰላም አስፈላጊ ነው ያሉት ደግሞ ሀጅ ኑሩ ኢብራሂም ናቸው። ነዋሪው የተፈጠረውን የሰላም እጦት በሁሉም ሰው ኑሮ ላይ ጫና መፍጠሩንም ተናግረዋል። የሰላም ጥሪው በግጭቱ ምክንያት የተፈጠሩ ችግሮች እንዲቀረፉ እድል ይሰጣልም ነው ያሉት።
ዘጋቢ፡- መሰረት ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!