
ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በክልሉ በርካታ አካባቢዎች ለወራት የዘለቀው ግጭት እና አለመረጋጋት ያደረሰው ውድመት መጠነ ሰፊ ነው፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠሩት ደም አፋሳሽ ግጭቶች የበርካቶችን ቤት እና ሕይዎት አደጋ ላይ ጥለው አልፈዋል፡፡ በጅራፍ ፋንታ አፈ ሙዝ ሲጮህባቸው የቆየ ትርፍ አምራች አካባቢዎች ወርቃማውን ጊዜ በሰቀቀን አሳልፈዋል፡፡
በክልሉ በተፈጠረው ግጭት ምክንያት የንግድ እንቅስቃሴ ከመቀዛቀዝ አልፎ ሙሉ በሙሉ የተዘጋባቸው ጊዜያትም አሉ፡፡ የቱሪዝም ዘርፉ ለዓመታት ከደረሰበት ጉዳት ማገገም በሚገባው ወቅት ሌላ ሳንካ ገጥሞት ሕይዎታቸውን በቱሪዝም ገቢ ላይ የመሠረቱ ወገኖች ለአደጋ ተጋልጠዋል፡፡ የትምህርት ተቋማት መተኪያ የሌለውን የተማሪዎቻቸውን ወርቃማ ጊዜ በአግባቡ ሳይሸፍኑ እንደተዘጉ ከርመዋል፡፡
በክልሉ ሕዝብ እና መንግሥት ላይ ዘርፈ ብዙ ፈተናዎችን የፈጠረውን የፀጥታ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት እና የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ለማጽናት የሚያስችል “የሰላም ጥሪ” ተላልፏል፡፡ ለተከታታይ ሰባት ቀናት በሚቆየው እና ሁለተኛ ቀኑን ባስቆጠረው የሰላም ጥሪ በርካቶች የክልሉን ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄ እና ፍላጎት በማክበር በጎ ምላሽ እየሰጡ ነው ተብሏል፡፡
የሰላም ጥሪውን ስኬታማ ለማድረግ እና የክልሉን የፀጥታ ሁኔታ በዘላቂነት ለማሻሻል የሚያስችል የውይይት መድረክ ተካሄዷል፡፡ በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የአሥተዳደር ጉዳዮች ዘርፍ ተቋማት የሰላም ጥሪው ስኬታማ እንዲኾን የሚያስችል ተግባራዊ ምላሽ ሊኖር ይገባል ብለዋል፡፡ የሰላም ጥሪው የይቅርታ ሂደትንም የሚከተል በመኾኑ የተሳሳተ እና የተዛባ ትርጉም እንዳይሰጠው በየደረጃው ያለን ፈጻሚ ግልጽ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡
የክልሉ መንግሥት የሕዝብን ጥያቄ አዳምጦ ተግባራዊ ምላሽ መስጠቱ አበረታች ሂደት ነው ያሉት ተወያዮቹ ከአፈጻጸም ጉድለት እና ትጋት የሚቀር ውስንነት እንዳይኖር መሥራት ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡ ተወያዮቹ የሰላም ጥሪውን የሚቀበሉ የታጠቁ ኃይሎች የክልሉ ሕዝብ አቅም ለማድረግ ተከታታይነት ያለው ሥራ መሥራት ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡
የሰላም ጥሪው የታለመለትን ዓላማ እንዲመታ ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎን በክልሉ ዘላቂ እና አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን መሥራት ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡ የክልሉ ዘላቂ ሰላም የሚጸናው በክልሉ የፀጥታ መዋቅር አቅም መኾኑን በመቀበል መንግሥት እና ሕዝቡ የፀጥታ ተቋማትን በማጠናከር ሊሠሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የሰላም ጥሪው ስኬታማ እንዲኾን ሰላምን የግጭት መቋጫ አድርጎ መውሰድ ይገባል ያሉት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማእረግ የአሥተዳደር ጉዳዮች ዘርፍ አስተባባሪ እና የሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ኀላፊ ደሳለኝ ጣሰው ናቸው፡፡ የተጀመረው የሰላም ጥሪ ስኬታማ እንዲኾን የአሠራር ሥርዓት መዘርጋት እና የሰላም ካውንስል ማቋቋም ይገባል ብለዋል፡፡
በአፍራሽ ኃይሎች የተዛባ መረጃ የተሳሳቱ ወንድሞቻችን እውነቱን ለማስረዳት የሰላም እሴት ግንባታን ማስረጽ ያስፈልጋል ያሉት ኀላፊው ለሰላም ቅድሚያ የሚሰጡ የታጠቁ ኃይሎችን ተቀብሎ ወደ ተሃድሶ ሥልጠና ማስገባት የቀጣይ ጊዜ የትኩረት አቅጣጫ ይኾናል ብለዋል፡፡ የሰላም ጥሪውን የተቀበሉ እና የተሃድሶ ሥልጠናውን የወሰዱ ወገኖቸቻችን በቀጣይ በተለያዩ መስኮች ስምሪት መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የሲቪል ሰርቪስ ቢሮን ጨምሮ ዛሬ በአሥተዳደር ጉዳዮች ዘርፍ ያሉ ተቋማት ውይይትም ተቋማቱ የሚጠበቅባቸውን ኀላፊነት እንዲወጡ ግልጸኝነት ለመፍጠር ያለመ ነው ብለዋል፡፡
በውይይቱ ሲቪል ሰርቪስ ቢሮ፣ ፍትሕ ቢሮ፣ ፀረ-መስና ኮሚሽን፣ ፖሊስ ኮሚሽን፣ ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት፣ ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን እና ርእሰ መሥተዳድር ጽሕፈት ቤት ተሳታፊዎች ነበሩ፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!