
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአፍሪካ የሚያጋጥሙ የደኅንነት ሥጋቶችን ለመቀልበስ የጋራ ትብብር እንደሚያስፈልግ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል 88ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል “በመስዋዕትነት አገርን የዋጀ የኢትዮጵያ አየር ኃይል” በሚል መሪ ኃሳብ ከሕዳር 20 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ እየተከበረ ይገኛል።
የመርኃ ግብሩ አንድ አካል የሆነው የአፍሪካ አየር ኃይል አዛዦች ፎረም በመካሄድ ላይ ነው።
በፎረሙ የአፍሪካ ሀገራት አየር ኃይል አዛዦች፣ የተለያዩ አገራት የአቪዬሽን ተቋማት ኃላፊዎችና ወታደራዊ አታሼዎች ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የረጅም ዓመት ታሪክ ያላትና ቅኝ ያልተገዛች ሀገር ናት ብለዋል።
አየር ኃይሉ በርካታ የአፍሪካ አገራትን በአየር ኃይል፣ በልምምድና በአየር ትራንስፖርት ዘርፎች እገዛ ሲያደርግ እንደቆየ ጠቁመው ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
አሁን ላይ ሀገራት የተለያዩ ችግሮች እያጋጠማቸው መሆኑን ጠቅሰው፤ እነዚህን ችግሮች ለመከላከልና ለመቋቋም በትብብርና በአጋርነት መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ያዘጋጀው ፎረምም የአፍሪካ አገራት የአየር ኃይሎቻቸውን አቅም በጋራ ለማስተባበርና ቅንጅታዊ አሰራርን ለማጠናከር አስተዋጽዖ ያደርጋል ብለዋል።
ይህም አፍሪካ አሁን ላይ እያጋጠማት ያለውን የጋራ የደኅንነት ሥጋቶች ለመከላከል እንደሚያስችል ነው የጠቆሙት።
ፎረሙ በተለይም የልምድ ልውውጥ ለማጠናከርና የባለሙያዎች ልውውጥ ለማድረግ እንደሚያስችልም ነው የጠቆሙት። በፎረሙ የተሳተፉ የዘርፉ አካላት ከኢትዮጵያ አየር ኃይል ጋር በትብብር ለመሥራት ቁርጠኛ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በፎረሙ ለተሳተፉ ለተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የአየር ኃይል አዛዦች ዕውቅና መሰጠቱን ኢዜአ ዘግቧል። እውቅናውን የመከላከያ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይና የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መረዳሳ አበርክተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!