
ባሕር ዳር፡ የካቲት 12/2012 ዓ.ም (አብመድ) በምዕራብ ጎጃም ዞን ቋሪት ወረዳ ቋሪት ኢየሱስ ቀበሌ ዳሞት ተራራ አካባቢ በረዶ ቀላቅሎ የዘነበ ዝናብ በሰብል፣ በመጠለያ እና በእንስሳት ላይ ጉዳት አድርሷል፡፡
የቋሪት ወረዳ የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሠለሞን በቀለ እንደገለጹት ትናንት የካቲት 11/2012ዓ.ም ከቀኑ 9፡00 ገደማ በጣለው ዝናብ በሰብል፣ በመጠለያ ቤቶችና በእንስሳት ላይ ጉዳት አድርሷል ብለዋል፡፡
የወረዳው ግብርና ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ አማረ ባይለው ጉዳቱ በደረሰ በ30 ደቂቃ ልዩነት ወደ ስፍራው እንደሔዱ ገልጸው ከፍተኛ መጠን ያለው በረዶ እንደጣለ መመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡ ከ25 እስ 30 ሄክታር በሚሸፍን መሬት ላይ በረዶ የቀላቀለው ዝናብ መዝነቡንም ነው የተናገሩት፡፡
ይህም በቀሪ እርጥበት በተዘሩት ጓያ እና ሽምብራ እንዲሁም በመስኖ ሰብሎች ላይ ጉዳት አድርሷል ብለዋል፡፡ በሰው ላይ ግን ጉዳት አለመድረሱን ነው ያስታወቁት፡፡
የጉዳት መጠኑን በማረጋገጥ ውሳኔ ለመስጠት መረጃ የሚያጣራ ባለሙያ መላካቸውንም አቶ አማረ ገልጸዋል፡፡
የአማራ ክልል አደጋ መከላከል፣ ምግብ ዋስትና ፕሮግራም እና ልዩ ድጋፍ የሚሹ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ወይዘሮ እታገኝ አደመ ደግሞ መረጃው እንዳልደረሳቸው ነው የተናገሩት፡፡
በወረዳው አስተዳዳሪ የሚመራ የተቋቋመ ግብረ ኃይል ስላለ ችግር ሲፈጠር የጉዳት መጠኑን በመለዬት ለክልሉ እንደሚልክም ተናግረዋል፡፡ መረጃውን መሠረት በማድረግ የክልሉን ድጋፍ የሚሻ ከሆነ ኮሚሽኑ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አስታውቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ