
ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሜን ወሎ ዞን ቆላማ ቀጣናዎች ኮማንድ ፖስት የክልሉ መንግሥት ያወጣውን የሰላም ጥሪ ተከትሎ በዞኑ ከተመረጡ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና ከወረዳ አመራሮች ጋር ምክክር አድርጓል።
በምክክር መድረኩ የሰሜን ወሎ ዞን አሥተዳዳሪ አራጌ ይመር እና የሰሜን ምሥራቅ እዝ ምክትል አዛዥ እና የኮማንድ ፖስቱ ሰብሳቢ ሜጄር ጀኔራል ሻምበል ፈረደን ጨምሮ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ተሳትፈዋል፡፡
የሰሜን ወሎ ዞን አሥተዳዳሪ አራጌ ይመር የአማራን ሕዝብ ጥያቄ ለማስመለስ ሞት ተገቢ አይደለም ብለዋል። የሕዝቡን ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ ማስመለስ ተገቢ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ ልጆቻችንን ከገቡበት የሞት ቀጣና እንዲወጡ እና የሰላም ጥሪ እድሉን እንዲጠቀሙ አበክረን ልንሥራ ይገባል ነው ያሉት። መድረኩ ላይ የተሳተፉ አካላት ሚናቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል፡፡
ከኮማንድ ፖስቱ እና በየወረዳው ከሚቋቋመው የሰላም ኮሚቴ፣ የህክምና ኮሚቴዎች እና ሌሎች አደረጃጀቶች ውስጥ በመቀናጀት የሰላም ጥሪውን ተቀብለው ለሚመጡ አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ የመንግሥትን ተግባር ልትደግፉ ይገባል ሲሉ አሥተዳዳሪው ገልጸዋል።
የኮማንድ ፖስቱ ሰብሳቢ ሜጀር ጀኔራል ሻምበል ፈረደ በኃይል እና በጉልበት የሚፈታ ጥያቄ የለም። አማራ ክልል ባለፉት ወራት ባሳለፈው ጦርነት ተጎድቷል ነው ያሉት። የጦርነት ማሳረጊያም ሰላም ነውና ብዙ ጉዳት ከመድረሱ በፊት የሰላም ጥሪውን መጠቀም የተሻለ መኾኑን ገልጸዋል።
የሰላም ጥሪው የአሸናፊነት እና የተሸናፊነት ጉዳይ ሳይኾን የክልሉን ሰላም የማረጋገጥ ጉዳይ በመኾኑ የተሰጠውን አጭር ጊዜ የታጠቁ ኃይሎች እንዲጠቀሙበት እና የኮማንድ ፖስት ቀጣናው ማኅበረሰብም ሚናውን እንዲወጣ አሳስበዋል። የተሰጠው የሰላም እድል ለክልሉ መረጋጋት መፍትሔን የሚያሳይ መኾኑን የውይይቱ ተሳታፊዎች አንስተዋል።
በመኾኑም በተሰጠው ቀን ወንድሞቻችን እና ልጆቻችን ወደ ሰላም እንዲመለሱ እንሠራለን ብለዋል።
የሰላም አዋጅ መታወጁ የመንግሥት ፍላጎት በይፋ ያሳወቀበት ስለኾነ ለሽማግሌዎች ትልቅ በር በመኾኑ የሽምግልና ሥራችንን እንቀጥላለን። ነገር ግን ለሰላም ሥንጥር ጦርነት ሊቆም ይገባል ብለዋል።
የሰባት ቀን ጊዜ ገደብ አጭር መኾኑን የገለጹት የውይይቱ ተሳታፊ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች የሰላም ጥረት ሂደት ላይ መሰናክል ሊኾኑ የሚችሉ ሌሎች ጉዳዮችንም ጠቅሰው የጋራ መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል
ዘጋቢ:- ካሳሁን ኀይለሚካኤል
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!