
ደብረ ብርሃን: ታኅሳሥ 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አሁን ያለው የሰላም እጦት የአካል ጉዳተኞችን ሕይወት የበለጠ እያወሳሰበ መኾኑን የሰሜን ሸዋ ዞን አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን አስታውቋል።አሚኮ ያነጋገራቸው የአካል ጉዳተኞች እንደሚሉት ደግሞ በገጠራማ አካባቢዎች ችግሮች ጎልተው ይታያሉ።
የሰሜን ሸዋ ዞን አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን ሰብሳቢ ጌታሰው ፋንታሁን አካል ጉዳተኞች ተገቢውን ድጋፍ እንዲያገኙ በማድረግ በኩል አኹንም መሰረታዊ ክፍተት መኖሩን ጠቁመዋል። ይህም አካል ጉዳተኞች ለሀገር ሊያበረክቱ የሚችሉትን አስተዋጽኦ በውል ካለመገንዘብ የመጣ እንደኾነ አመላክተዋል።
በየጊዜው የሚያጋጥሙ የሰላም እጦት ችግሮች አካል ጉዳተኞችን ይበልጥ ለችግር ተጋላጭ ሲያደርጉ ይስተዋላል። አቶ ጌታሰው እንደሚሉትም በሰሜን ሸዋ ዞን አኹን ላይ በርካታ ወገኖች በጦርነት ምክንያት ለአካል ጉዳት እየተጋለጡ ይገኛሉ።
የሰሜን ሸዋ ዞን ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ የሮምነሽ ጋሻው በአካል ጉዳተኞች ላይ ያለው አመለካከት በተወሰነ መልኩም ቢኾን መሻሻል ታይቶበታል ነው ያሉት። ይኹን እንጂ ከተረጂነት አስተሳሰብ እንዲወጡ የማድረግ ተግባሩ አኹንም ክፍተት ያለበት ነው፤ ይህም ብዙዎች በማኅበራዊ ቀውስ ውስጥ እንዲኖሩ አድርጓል ብለዋል።
ማኅበራዊ ቀውሱን ለማስቀረት ጦርነት ማብቃት አለበት ያሉት የሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊዋ ወይዘሮ የሮምነሽ ከቤተሰብ ጀምሮ ስለሰላም መምከር እና ወደ ተግባር መግባት እንደሚገባ አንስተዋል። በሰሜን ሸዋ ዞን ከ300 ሺህ በላይ አካል ጉዳተኞች እንደሚገኙ የዞኑ ሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ መረጃ ያመለክታል።
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!