
ደሴ: ታኅሳሥ 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል እንስሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት በምሥራቅ አማራ ዞኖች እና ወረዳዎች ለሚገኙ ባለሙያዎች የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠና በኮምቦልቻ ከተማ እየሰጠ ይገኛል።
በሥልጠናው ላይ በምሥራቅ አማራ ዞኖች እና ወረዳዎች የሚገኙ የእንስሳት ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት ባለሙያዎች እየተሳተፉ ነው፡፡ ሥልጠናው የፈጻሚዎችን አቅም የሚያዳብር እና የእንስሳትን ዝርያ በማሻሻል እንደ ሀገር የወተት ምርታማነት የሚያሳደግ እንደኾነ ተገልጿል፡፡
የአማራ ክልል እንስሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት የወተት ሃብት ባለሙያ ደመላሽ አይችሌ ሥልጠናው ለፈጻሚ ባለሙያዎቹ በክልሉ በተለያዩ ክላስተሮች እየተሰጠ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ እንደ ሀገር ካለውን የእንስሳት ቁጥር አንጻር የተሻሻሉ ዝርያዎች ጥቂት በመኾናቸውን ለማሻሻል ታስቦ መኾኑንም ጠቁመዋል፡፡
የክልሉን ምርታማነት ከማሳደግ አኳያ ከሚስተዋሉ ችግሮች መካከል የተሻሻለ የእንስሳት ዝርያ አናሳ መኾን፣ የእንስሳት ጤና እና የመኖ አለመሟላት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡
ችግሮቹን ለመቅረፍ ሥልጠናው ጠቃሚ እንደኾነ የገለጹት የአማራ ክልል እንስሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት የእንስሳት መኖ ልማት እና አጠቃቀም ዳይሬክተር መኳንንት ዳምጤ ናቸው። ሥልጠናው በቀጣይም ከፈጻሚ ባለሙያዎች በተጨማሪ ውጤታማ ለኾኑ የእንስሳት አርቢዎች እንደሚሰጥ ተገልጿል።
ዘጋቢ፡- ደምስ አረጋ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!