ከ116 ሺህ በላይ በአስገድዶ መድፈር እና መሰል አደጋ ተጋላጭ ለኾኑ ዜጎች በተለያዩ አገልግሎቶች ተደራሽ ማድረጉን ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ገለጸ።

187

አዲስ አበባ: ታኅሳሥ 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአንድ ዓመት ብቻ ከ116 ሺህ በላይ በአስገድዶ መድፈር እና መሰል አደጋ ይበልጥ ተጋላጭ ለኾኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች በተለያዩ አገልግሎቶች ተደራሽ ማድረጉን ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ገልጿል።

በሕጻናት ጥበቃ እና ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን መከላከል ላይ ሀገር አቀፍ ውይይት እየተካሄደ ነው። ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር ባዘጋጀው መድረክ በኢትዮጵያ በሕጻናት ጥበቃ እና ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን መከላከል ላይ የተገኙ ተሞክሮዎች ልውውጥ የማድረግ ዓላማ አለው።

ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በመኾን በኢትዮጵያ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን እየተገበረ ይገኛል። በዋነኝነት በሕጻናት ጥበቃ እና ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን መከላከል የሚያስችሉ ሰብዓዊነትን ማዕከል ያደረጉ የበጎ አድራጎት ሥራዎች በአማራ፣ በትግራይ፣ በኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በቀድሞው የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል እንዲሁም በአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ሲሠራ ቆይቷል፡፡

ድርጅቱ በ68 አካባቢዎች እ.አ.አ ከ2022 እስከ 2023 የሠራቸውን ሥራዎች ከአጋር አካላት ጋር በመኾን ገምግሞ የተሞክሮ ልውውጥ አድርጓል። በተለይ በሰሜኑ ጦርነት በአስገድዶ መድፈር እና መሰል አደጋ ለተጎዱ የማኅበረሰብ ክፍሎች ትኩረት ተሰጥቷቸው ድጋፍ ሲደረግላቸው እንደነበር ተገልጿል።

በአንድ ዓመት ብቻ ከ116 ሺህ በላይ የማኅበረሰብ ክፍሎችን በተለይም ይበልጥ ተጋላጭ የኾኑትን በተለያዩ አገልግሎቶች ተደራሽ ማድረጉን የወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ካንትሪ ዳይሬክተር ሚስ ካርመን ቲል ገልጸዋል።

ከቤተሰቦቻቸው በተለያዩ ምክንያቶች የተለያዩ 1ሺህ 843 ሕጻናትን ከቤተሰቦቻቸው ጋር ማገናኘት መቻሉን የወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ የሕጻናት እና ሴቶች ጥበቃ ዳይሬክተር እሸቱ ዓለሙ (ዶ.ር) ገልጸዋል፡፡

ከ40 በመቶ በላይ ሕጻናት ያለእድሜ ጋብቻ ይጋለጣሉ፤ ለዚህ መንግሥት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል ዳይሬክተሩ። በውይይቱ ከሴቶች እና ሕጻናት፣ ከጤና ሚኒስቴር፣ ከክልል የመጡ የሥራ ኀላፊዎች፣ ሌሎች ዓለም አቀፍ ረጅ ድርጅቶች፣ ሀገር በቀል የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

ዘጋቢ:- ድልነሳ መንግሥቴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የትራንስፖርት ዘርፍ መጎዳት ያመጣቸው ችግሮችን ለመፍታት አይነተኛ መንገድ ሰላምን ማስቀደም ነው” የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ባለሥልጣን
Next article“ከእንስሳት የሚገኘውን ተዋጽኦ ለማሳደግ የእንስሳትን ዝርያ ማሻሻል ይገባል” አማራ ክልል እንስሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት