
ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሰላም እጦት የፈተነው የትራንስፖርት ሥራ ብዙዎችን ለኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ ቀውስ መዳረጉን የአማራ ክልል የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ባለሥልጣን አስታውቋል።
በአማራ ክልል የተፈጠረው የሰላም መናጋት ዘርፈ ብዙ ቀውስ እያስከተለ ነው። በትራንስፖርት ዘርፉ ላይ እየደረሰ ያለው ችግርም ተደራራቢ ችግሮችን አስከትሏል። አቶ ደመላሽ ስንሻው በአማራ ክልል ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ናቸው።
ሰላም የሁሉም መሠረት ቢኾንም ትራንስፖርት ደግሞ በተለየ ኹኔታ ሰላምን ይፈልጋል ይላሉ። መሪ ጨብጠው ሰዎችን ካሰቡበት የሚያደርሱ አሽከርካሪዎች ደኅንነትን አጥብቀው ይፈልጋሉ፡፡ ሰላም ካልተሰማቸው ግን ሕይዎቱን አምኖ የሰጣቸውን ተሳፋሪ አደጋ ላይ ይጥላሉ።
በተጨማሪም በየቦታው እና መንገዱ የሚደርሰው እንግልት ቀጥተኛ ገፈት ቀማሽ በትራንስፖርት ዘርፍ የተሠማሩት በመኾናቸው ሰላም ከሌለ ሥራው ይቆማል ይላሉ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊው። በክልሉ የተፈጠረው የሰላም መደፍረስ የትራንስፖርት ሥራው እንዲስተጓጎል አድርጎታልም ብለዋል።ይህም ምጣኔ ሃብታዊ እና ማኅበራዊ ቀውስ አስከትሏል።
ሰዎች ታመው ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው መታከም አልቻሉም፤ በትራንስፓርቱ ዘርፍ ተሰማርተው የዕለት ጉርሳቸውን የሚያገኙ ወገኖችም ኑሮ ዳገት ኾኖባቸዋል። ባለሃብቶች፣ አሽከርካሪዎች እና ረዳቶች ገቢያቸው ቆሞ በኑሮ እንዲፈተኑ ምክንያት ኾኗል እንደ አቶ ደመላሽ ገለጻ።
ሸቀጣ ሸቀጦችን ከቦታ ቦታ ማንቀሳቀስ አልተቻለም፤ የአርሶ አደሩ ምርትም ገቢያ አልደረሰም፤ የግብርና ግብዓቶች በተፈለገው ጊዜና መጠን ለማድረስም አልተቻለም።ይህ ሁሉ ተደምሮ የኑሮ ውድነቱ አባብሶታል፤ በልቶ ማደር ፈታኝ ኾነ ብለዋል የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊው።
ችግሩ በምዕራቡ የአማራ ክልል የባሰ ነበር ያሉት አቶ ደመላሽ መንገድ ድንገት ተከፍቶ ድንገት ስለሚዘጋ ሰዎች ወጥተው መመለስ ባለመቻላቸው በብዙ እየተፈተኑ መኾኑን አንስተዋል።
ሌሎች ደግሞ ይህን በመፍራት በደሰታ እና በሀዘን የሚጠበቅባቸውን ማኅበራዊ ሕይዎት ባለመወጣታቸው ማኅበራዊ ቀውስ እየደረሰባቸው ነው።
የክልሉ ወደ ሰላም መመለስ በተለይ በትራንስፖርቱ ዘርፍ ላይ ለተከሰተው ችግር አይነተኛ መፍትሔ እንደኾነም አቶ ደመላሽ አስረድተዋል። የዘርፉ መጎዳት ያመጣቸው ችግሮችን ለመፍታት አይነተኛ መንገድ ሰላምን ማስቀደም መኾኑን አንስተዋል።
በአስማማው አማረ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!