
ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ላለፉት አራት እና አምስት ወራት ገደማ ክልሉ የነበረበት የጸጥታ እና ሰላም እጦት ችግሮች የክልሉን ሕዝብ እና መንግሥት በብዙው ጎድተውታል። ሰብዓዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ፣ ሥነ ልቦናዊ እና ማኅበረሰባዊ ስብራቶች ክልሉን የፈተኑ ችግሮች ኾነው አልፈዋል።
የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት እና የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ለማጽናት የክልሉ መንግሥት የሰላም ጥሪ አስተላልፏል። የሰላም ጥሪው ውጤታማ እንዲኾን የሚያስችል ውይይት እና ምክክር የክልሉ የአሥተዳደር ጉዳዮች ዘርፍ ተቋማት እያደረጉ ነው።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማእረግ የአሥተዳደር ጉዳዮች ዘርፍ አስተባባሪ እና የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ ደሳለኝ ጣሰው ባለፉት ወራት ክልሉ ያለፈበት መንገድ እጅግ ፈታኝ እና አደገኛ ነበር ብለዋል።
የችግሩ ምንጭ ውስብስብ ምክንያት እና ዘርፈ ብዙ ተሳትፎ የታየበት እንደነበር ያነሱት አቶ ደሳለኝ በሀገር መከላከያ ሠራዊት እና በክልሉ የጸጥታ ኀይሎች የጋራ ርብርብ የኅልውና ስጋቱ መቀልበስ ተችሏል ነው ያሉት። ምንም እንኳን ችግሩ ቢቀለበስም ጥሎት ያለፈው የሞራል ስብራት፣ የእሴት መሸርሸር፣ የምጣኔ ሃብታዊ ጉዳት እና ማኅበረሰባዊ ሳንካ በቀጣይም ፈታኝ ኾኖ ይቆያል ብለዋል።
እንደ አቶ ደሳለኝ ገለጻ ላለፉት ሦስት አስርት ዓመታት በአማራ ሕዝብ ላይ የተፈጠረው የሴራ ፖለቲካ ጉዳት ሥነ ልቦናዊ ጫና በአግባቡ ሳያገግም ተደጋጋሚ ክልላዊ ፈተናዎች ተከስተዋል። በቅርቡ የተፈጠረው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት እና ወረራ ግጭትን ብቻ የመፍትሔ አማራጭ አድርጎ የመመልከት እሳቤን እያለማመደ መጥቷል ነው ያሉት።
ጭካኔ የተሞላበት ሰብዓዊ ጥቃት እና ወንጀልን መለማመድ ከወረራው የተወረሱ ሥነ ልቦናዊ ልምምዶች እየኾኑ መምጣታቸውን አንስተዋል አቶ ደሳለኝ። ችግሩ እያደገ መጥቶ መንግሥታዊ ሥርዓትን በኀይል ለመጣል እስከ መሞከር ተደርሷልም ነው ያሉት። ይህን መሰሉ ተገቢ ያልኾነ ልምምድ ከወዴት እንደመጣ ይታወቃልም ብለዋል።
ግጭት ተፈጥሯዊ ክስተት መኾኑ ይታወቃል ያሉት አቶ ደሳለኝ በየትኛውም ዓለም ግን “ግጭት በጦርነት ተጠናቅቆ አያውቅም፤ የሰላም አማራጮችን ማየት ያስፈልጋል ” ነው ያሉት። ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባትም የክልሉ መንግሥት በሆደ ሰፊነት የሰላም ጥሪ ማስተላለፉን አንስተዋል።
በክልሉ የተፈጠረው ሰብዓዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ እና ማኅበራዊ ጉዳት ቀላል እንዳልኾነ ቢታወቅም የከፋ ችግር ሳይፈጠር የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ለማጽናት የሰላም ጥሪው አስፈላጊ ነበር ተብሏል። የሰላም ጥሪው የተሳካ እንዲኾን ተቋማት ሚናቸው የጎላ እንደሚኾንም አቶ ደሳለኝ አንስተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!