
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 03/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሰላም መከራን ትቋጫለች፤ ደስታን ታመጣለች፤ ፍቅርን ታድላለች፤ የደም መፍሰስን፣ የአጥንት መከስከስን፣ የሕይወት መቀጠፍን ታስቀራለች፤ ሰላም ባለች ጊዜ ነብሰ ጡሮች ይወልዳሉ፤ ሕጸናት ያድጋሉ፣ ያበቡት አዝእርት ያሸታሉ፤ ያሸቱት ያፈራሉ።
ሰላም ባለች ጊዜ የታመሙት ይታከማሉ፤ ታክመውም ፈውስን ያገኛሉ፤ ሰላም ባለች ጊዜ የተነፋፈቁት ይገናኛሉ፣ ሰላም ባለች ጊዜ እናት የልጆቿን ደስታ ታያለች፣ ልጆቿን አጎራብታ በልጅ ማዕረግ ትደምቃለች፤ ሰላም ባለች ጊዜ አባት በልጆቹ ይኮራል፤ በግርማቸው ይከበራል፡፡
ሰላም ባለች ጊዜ አረጋውያን ይጦራሉ፤ ለሕዝብ ፍቅር ይጸልያሉ፤ የሚያድጉትን ሕጻናትን ይመርቃሉ፤ ወግና ስርዓትን ያስተምራሉ፤ ሰላም ባለች ጊዜ በየመስጊዶቹ አዛን ይደረሳል፤ ሶላት ይሰገዳል፤ ሰላም ባለች ጊዜ በየአብያተ ክርስቲያናቱ፣ በየገዳማቱ ኪዳን ይደረሳል፤ ቅዳሴ ይቀደሳል፡፡ ሰላም ባለች ጊዜ የተጀመሩት ይፈጸማሉ፤ ያልተጀመሩት ይጀመራሉ፤ በሃሳብ የነበሩት በተግባር ይታያሉ፡፡
ሰላም ባለች ጊዜ ከተማዎች አይፈርሱም፤ ፋብሪካዎች አይወድሙም፤ ደሀዎች አይራቡም፤ አቅመ ደካሞች አይንገላቱም፤ ሰላም ባለች ጊዜ ረሃብ አይጠናም፤ ድህነት ሥር አይሰድም፤ ሰላም ባለች ጊዜ በሠርክ ማልቀስ፣ የሀዘን ካባ መልበስ አይኖርም፡፡ ሰላም ሁሉንም ትሰጣለች፤ ሰላም ሁሉንም አሸናፊ ታደርጋለችና፡፡
ሰላም በታጣ ጊዜ ንጹሐን ይሞታሉ፤ አረጋውያን ያለ ጧሪና ቀባሪ ይቀራሉ፤ እናቶች ያለቅሳሉ፤ ተስፋ የተጣለባቸው ወጣቶች በከንቱ ያልፋሉ፤ መንገዶች ይዘጋጋሉ፤ ሰላም በመታጣቱ ታክመው መዳን የሚችሉ ሕመሙን ሞተዋል፤ እናት ወሊድ ምክንያት ላይመለሱ አሸልበዋል፤ ፋብሪካዎች ፈርሰዋል፤ ለዘመናት የተገነቡ ከተሞች ተጎሳቁለዋል፤ ያመሩ ሕንጻዎች ወድመዋል፤ የብዙዎች የእንጀራ መሶብ የሆኑ ተቋማት እንዳልነበር ሆነዋል፤ እናት እና ልጅ ተለያይተዋል፡፡
ለወራት በዘለቀው የአማራ ክልል የሰላም እጦት እልፍ ነገር አሳጥቷል፡፡ ወንድምና ወንድም ተገዳድለዋል፤ ተስፋ የተጣለባቸው የልማት ሥራዎች ቆመዋል፤ አርሶ አደሮች ሰብላቸውን ለመሰብሰብ ተቸግረዋል፡፡
የአማራ ክልል መንግሥት ለወራት የቆዬው ግጭት እንዲበርድ፣ ደም እንዳይፈስስ፣ ሰላም በዘላቂነት እንዲመለስ በሚል የሰላም ጥሪ አቅርቧል፡፡ የሰላም ጥሪው ስለ ሕዝብ ሰላምን መምረጥ፣ ስለ ሰላም በአንድነት በመቀመጥ ሁሉንም አሸናፊ ማድረግን ያለመ ነው፡፡
የክልሉ መንግሥት በሰላም ጥሪውም “በክልሉ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ ከሕዝብ ጋር በተደረጉ ተከታታይ ውይይቶች የሕግ የበላይነትን ባረጋገጠ አግባብ ለታጣቁ አካላት የሰላም ጥሪ ቀርቦ ግጭቱ እንዲያበቃ እና አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን ከሕዝብ የተነሳውን ጥያቄ በመቀበል፤ ተጨማሪ ደም መፋሰስን፣ ጥፋትን እና ውድመትን ለማስቀረት መንግሥት የሰላም አማራጮችን አሟጦ የመጠቀም ጥረቱን ማስቀጠል ለሀገር እና ለሕዝብ ያለውን ጠቀሜታ ከግምት በማስገባት፤ የፖለቲካ አጀንዳ እና ጥያቄዎች በሰላማዊ እና ሕጋዊ መንገድ ብቻ ዘላቂ መፍትሔ እንደሚያገኙ፤ ለሰላማዊ የፖለቲካ ውይይት እና ምክክር መንገድ የሚጠርግ እርምጃ መውሰድ አስፈላጊ መሆኑን በማመን ነው” የሚል መልእክት አስተላልፏል።
የሰላም ጥሪውን መቀበል እና ጥያቄዎችን በውይይት መፍታት ከኪሳራ ያድናል፡፡ ከደም መፋሰስ፤ ሃብትና ንብረት ከመከስከስ ይታደጋል፡፡ በዓለም ላይ ጦርነት የጀመራቸው እልፍ ጥያቄዎች ነበሩ፡፡ ጦርነት ግን አልቋጫቸውም፡፡ የመጨረሻ መቋጫቸው ሰላምና ውይይት ነው፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን የጨረሰ ጦርነት የተቋጨው በሰላም ነው፡፡ መንግሥት ያፈረሰው፤ ዘርን ከዘር አለያይቶ ያጋደለውም የተቋጨው በሰላምና በውይይት ነው፡፡
የዓለም ኃያላን ሀገራት ጎራ ለይተው ከአንድም ሁለት ጊዜ የዓለም ጦርነቶች አካሂደዋል፡፡ በተካሄዱት ከባባድ የዓለም ጦርነቶች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ሞተዋል፡፡ በስልጣኔ አብበው የነበሩ ሀገራት ፈራርሰዋል፡፡ በጦርነቱ ቀጥተኛ ተሳታፊ ያልነበሩ ንጹሐንም አልቀዋል፡፡ የዚህ ሁሉ መቋጫው ግን ሰላም ነበር፡፡ ሀገራቱ ጦርነትን ጥለው ሰላምን በመረጡ ጊዜ ዓለም ወደ ሰላም ተመለሰች፡፡ ባዕዳን በሚባባሉ ሀገራት የተደረጉ ጦርነቶች እንኳን በሰላም ተቋጭተዋል፡፡ በወንድማማቾች መካከል የሚደረግ ጦርነትም በፍቅር ሊተካ ግድ ይለዋል፡፡ አስቀድሞ ነገር ወንድማማቾች ሊተባበሩ ይገባል እንጂ ሊገዳደሉ አይገባም ነበር፡፡
በወልድያ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ማብሬ ታዴ አንድነትን በሚያመጡ ጉዳዮች ላይ መሥራት ይገባል ይላሉ፡፡ አካታች የሆነ፣ ሁሉንም ኃይሎች በሰላማዊ መንገድ የሚያሳትፍ፣ ልዩነትን በሰላማዊ መንገድ መፍታት የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል ነው የሚሉት፡፡
በኢትዮጵያ ተስፋ እና እድሎች የነበሩባቸው ለውጦች ከ1950ዎቹ ጀምሮ እንደነበሩ የሚያስታውሱት መምህሩ በአካሄድ ሥህተት እና በሌሎች ምክንያቶች እድሎች አልፈዋል ነው ያሉት፡፡ እንደ መምህሩ ገለጻ የተፈጠሩ እድሎችን በአግባቡ አለመጠቀም በጦርነት አዙሪት ውስጥ ከትተዋል፤ ችግሮችን የበለጠ አወሳስበዋል፤ ሁልጊዜም እድል እያባከኑ መሄድ የተገባ አይደለም፤ ሁሉንም ነገር ይቅርብኝ ብሎ ሁሉንም ኃይሎች ይምጡ ብሎ መነጋገር ያስፈልጋል፤ በንግግር ባሕልን መቀየር ይገባል፤ በንግግር ለመፍታት መወሰን አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡
መሠረት ያለው እና ከሕግ የማይወጣ ውይይት ለዘላቂ ሰላም ወሳኝ ጉዳይ መሆኑንም አንስተዋል፤ በውይይት እና በምክክር ችግሮችን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ መፍታት ያስፈልጋልም ነው ያሉት፡፡ አንዳንድ ጊዜ ይላሉ መምህሩ ያለኝ ነገር ሁሉ ይቅርብኝ ብሎ ወደ ውይይት እና ወደ ምክክር መምጣት ይገባል ብለዋል፡፡ ሁሉም የያዘውን የፖለቲካ አቋም ይዞ በውይይት እንፍታው ብሎ መቀመጥ፤ መተማመን እና በንግግር መፍታት አዋጩ መሆኑንም ያነሳሉ፡፡
ጦርነት ሄዶ ሄዶ አንዱን አሸናፊ ሊያደርግ ይችላል፤ ሰላም እና ውይይት ግን ተሸናፊ የለውም፤ ሁሉም አሸናፊ ነው፤ ውይይት ሲኖር ችግር የሚፈተው ሁሉንም በሚያስማማ እና በሚጠቅም መንገድ ነውና፡፡ በየትኛውም ሀገር የፖለቲካ ቀውስ ይፈጠራል የሚሉት መምህሩ በእኛ ሀገር የተለመደው ችግሩን በዘላቂነት ከመፍታት ይልቅ፣ ለችግሩ ማስታገሻ እየሰጡ ማለፍ ነው ይላሉ፡፡ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ደግሞ ጥልቅ ውይይት እና ሰላም ያስፈልጋል ነው የሚሉት፡፡
ችግርን በኃይል ብቻ እፈታለሁ ማለት እንደተዳፈነ እሳት ማድረግ እንጂ፣ ጨርሶ መፍታት አይደለም፤ በሕግ አግባብ ተቀራርቦ፤ ሁሉንም በሚያግባባ መንገድ መፍታት ግን ተመራጩ እና አዋጩ ነው ብለዋል መምህሩ፡፡ ለዘላቂ ሰላም የውይይት እና የሰላም መርህም ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡
ኃይል የመጨረሻ አማራጭ እንጂ የመጀመሪያም አዋጭ መንገድም አይደለም የሚሉት መምህሩ የመጀመሪያው እና የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጠባሳ ጥለው የሄዱትም ለዚህ ነው ይላሉ፡፡ በኢትዮጵያ የተካሄደው የሰሜኑ ጦርነት ምን ያክል አክሳሪ እንደነበር ተመልከተናል፤ ጦርነት አክሳሪ ነው፤ ዘላቂም አይደለም ብለዋል።
እንደ መምህሩ ገለጻ የኃይል እርምጅ ሌላ የኃይል እርምጃን እየወለደ ይሄዳል፤ ትክክለኛም አይደለም፤ በኃይል የሚፈታ ነገር ጠባሳ እያመጣ የሚሄድ ነው፤ በሕግና በሥርዓት የሚፈታ ጉዳይ ግን ዘላቂ ነው፤ መጠቀም ያለብን ሰላማዊ የሆነ ውይይትን ብቻ ነው፤ የሰሜኑን ጦርነት ደም መፋሰስ ያቆመው ሰላማዊ ውይይት ስለተደረገ ነው፡፡ ሰላምን መምረጥ አዋጩ እና አትራፊው ነው ይላሉ፡፡
ለሰላም በተዘጋጁ ጊዜ ደም ይደርቃል፤ ጥል ይርቃል፡፡ ሁሉንም ለሰላም ስል ልተተው፣ ለሰላም ስል ይቅርብኝ፣ በእኔ ምክንያት ሰላም ከመጣች፣ ደም መፍሰስም ካቆመች ለሰላም ተዘጋጅቻለሁ ብሎ ሁሉም ራሱን ሊጠይቅ እንደሚገባ አስገንዝበዋል!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!