
ባሕር ዳር፡ የካቲት 12/2012 ዓ.ም (አብመድ) በማረሚያ ቤቶች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለማስቀረት የሚያግዝ የልምድ መለዋወጫ ምክክር በባሕር ዳር እየተካሄደ ነው፡፡
የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ጀማል አባሶ እንደገለጹት ከአሁን በፊት በሀገሪቱ በሚገኙ ማረሚያ ቤቶች የሰብዓዊ ጥሰቶች፣ ኢ-ህገመንግስታዊ አሠራሮች እና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ሲፈጸሙ ቆይተዋል፡፡ ችግሩን ለመፍታት ታራሚዎች፣ የፖሊስ አባላት እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት የተካተቱበት ጥናት ተደርጎ የለውጥ ሥራ መጀመሩን ኮሚሽነር ጀነራል ጀማል ገልጸዋል፡፡
ወደ ‹‹ሪፎርም›› ከተከባ ጀምሮ በሀገሪቱ ሰብአዊ ጥሰት ይፈጸምባቸው የነበሩ በሶማሌ ክልል የሚገኘው ማረሚያ ቤት እና የፌዴራል ፖሊስ የምርመራ ማዕከል የነበረው ‘ማዕከላዊ’ ተዘግተው በሙዚየምነት እንዲያገለግሉ መደረጉንም ኮሚሽነር ጀነራሉ አስታውሰዋል፡፡
በፌዴራል ማረሚያ ቤት “ጨለማ ቤቶች” እየተባሉ የሚጠሩ አሰቃቂ ሥራ ይፈጸምባቸው የነበሩትም ፈርሰው በአዲስ እንዲገነቡ ተደርጓል ነው ያሉት፡፡ ጨለማ ቤቶችም ግልጽ እንዲሆኑ እና በማረም እና ማነጽ ሥራ ላይ አተኩረው እንዲሰሩ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡
በሀገሪቱ በሁሉም ማረሚያ ቤቶች ተግባራዊ የሚደረግ የማረም እና የማነጽ መተዳደሪያ ደንብ መዘጋጀቱን የተናገሩት ኮሚሽነሩ በዚሁ መድረክ ይጸድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል፡፡
ጉባኤውም የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዳይደገሙ ተሞክሮዎችን ለመጋራት ትልቅ ፋይዳ እንዳለው በምክክሩ የተሳተፉ ኮሚሽነሮች ተናግረዋል፡፡
11ኛው ፌዴራል እና የክልል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ኮሚሽነሮች የጋራ የምክክር ጉባኤ “የህግ ታራሚዎችን ሰብአዊ መብት በማክበር፣ የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ ውጤታማ የማረም እና ማነጽ ተግባራችን የተጀመረውን የማረሚያ ተቋማት ሪፎርም እናሳካለን” በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሰራ