
ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 03/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በምክትል ርዕሰ መሥተዳድር ማእረግ የአማራ ክልል ከተሞች ዘርፍ ክላስተር አሥተባባሪ እና የከተማ መሰረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር)በተያዘው በጀት ዓመት በአማራ ክልሉ በሚገኙ ከተሞች የነዋሪዎችን የቤት ችግር ለመቅረፍ 44 ሺህ ቤቶች ይገነባሉ ብለዋል፡፡
እንደ ዶክተር አሕመዲን ገለጻ ቤቶቹ በሪልስቴት፣ በማኅበራት በማደራጀት፣ ለግለሰቦች የቤት መስሪያ ቦታ በመስጠት እንዲሁም በመንግሥት የሚገነቡ ናቸው፡፡
በከተሞች የመኖሪያ ቤት አቅርቦት መሠረታዊ ችግር ነው ያሉት ዶክተር አሕመዲን በክልሉ በሚገኙ ከተሞች ያለውን የቤት አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ ፈጣን የኾኑ የግንባታ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በአጭር ጊዜ ተገንብተው ለነዋሪዎች እንዲተላለፉ ታቅዶ እየተሠራ መኾኑን ከኢፕድ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል፡፡
ዶክተር አሕመዲን አክለውም የሚገነቡት ቤቶች በታቀደላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ ለቤት መስሪያ ግብዓት ከማሟላት አንጻር ሰፋፊ ሥራዎች እየተሰሩ ነው ሲሉ ገልጸዋል። በተጨማሪም ለቤት ግብዓት የሚኾኑ አምራች ኢንዱስትሪዎች እየተገነቡ መኾኑን ተናግረዋል፡፡
ጎንደር እና ባሕር ዳር ከተሞች ላይ ፈጣን የኮንክሪት ማምረቻ ቴክኖሎጂ እንዲሁም ደብረ ብርሃን ከተማ ላይም ለቤት ግንባታ የሚውል ካናል ማምረት የሚያስችል ኢንዱስትሪ ወደ ሥራ ገብቷል ያሉት ዶክተር አህመዲን እነዚህን ጅምር ተግባራት ወደ ውጤት መቀየር እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡
በክልሉ ለቤት መስሪያ ብለው ቦታ ወስደው ለተለያየ አገልግሎት በሚያውሉ አካላት ላይ ክትትል እንደሚደረግም ነው ዶክተር አሕመዲን የገለጹት፡፡
የቤት ግንባታ ጋር ተያይዞ የራሱ የአሰራር መመሪያ ይፈልጋል ይንንም በሚመለከት የአሰራር ሥርዓት እየተዘጋጀ ነው ብለዋል፡፡
እንደ ዶክተር አሕመዲን ገለጻ በክልሉ ስምንት የ”ጂኦ ፖሉታንት” ከተሞች አሉ ያሉ ሲሆን በከተሞቹ የነገውን ትውልድ ጥቅም የሚያስከብር እና ለአደጋ የማያጋልጥ ስትራቴጂክ እቅድ እየተዘጋጀ ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡
በስምንቱ ከተሞች መዋቅራዊ ፕላን ሲዘጋጅ ቴክኖሎጂ፣ ዲጂታላዜሽን እንዲሁም ስማርት ሲቲን ታሳቢ ያደረገ ሥራ እንዲሰሩ የክልሉ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
በከተሞቹ የነዋሪውን ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ችግሮች ለመቅረፍ የመሰረተ ልማት ሥራዎች የተሟሉ እንዲኾኑ በተለይ የመንገድ መሠረተ ልማቶች በተለመደው መንገድ መሥራት ብቻ ሳይኾን ቴክኖሎጂን ታሳቢ ባደረገ መልኩ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
ባሕር ዳር፣ ደብረ ብርሃን፣ ጎንደር፣ ደሴ፣ ወልዲያ፣ ደብረ ታቦር፣ ደብረ ማርቆስ እና ኮምቦልቻ በክልሉ ወደ “ስማርት” ከተማነት ከሚያድጉ ከተሞች መካከል ናቸው፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!