ወታደራዊ አታሼዎች የብላቴ የኮማንዶና አየር ወለድ ማሠልጠኛ ማዕከልን ጎበኙ።

28

ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 03/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ወታደራዊ አታሼዎች በብላቴ ኮማንዶና አየር ወለድ ማሠልጠኛ ማዕከል በመገኝት የሥልጠና ፣ የመሰረተ ልማትና አጠቃላይ የማሠልጠኛውን የሥልጠና እንቅስቃሴ ተመለከቱ።

በኢትዮጵያ የዩናይትድ ኪንግደም አታሼ ኮሎኔል ማርክ ባቫን የኮማንዶ፣ አየር ወለድ እና ልዩ ኃይልና ፀረ ሽብር ሥልጠና አሰጣጥ ሂደት ውስብስብ የኾነ ግዳጅን ለመወጣት የሚያስችል መኾኑን ገልጸዋል።

ዘመናዊ የኾነ የሥልጠና መሰረተ ልማት መኖሩ ሠልጣኞችን በብቃት እና በጥራት አሠልጥኖ ለማብቃት አጋዥ መኾኑን አስረድተዋል፡፡

በቀጣይም ሀገራችን ከኢትዮጵያ ጋር በወታደራዊ መስክ በማቴሪያልና በተለያዩ መስኮች የጋራ አቅምን ለማሳደግና ለማጠናከር በትብብርና በአንድነት እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል፡፡

በጉብኝቱ ዕለት በአመራሮች ለተደረገላቸው አቀባበልና ገለፃ ላቅ ያላ ምሥጋና አቅርበው በዚህም ደስተኛ መኾናቸውን ተናግረዋል፡፡

የኮማንዶና አየር ወለድ ማሠልጠኛ ማዕከል አዛዥ ኮሎኔል ቦጃ አጋ ስለ ማሠልጠኛ ማዕከሉ አጠቃላይ ነባራዊ ሁኔታ እና ሥለ ሥልጠና አሠጣጥ ሂደቱ ለእንግዶች ገለፃ አድርገዋል።

ከመከላከያ ጋር አብረው መሥራት ከሚፈልጉ ሀገራት ጋር በጋራ መሥራት ሽብርተኞችን ለማጥፋት እና ተሞክሮን ብሎም ልምድን ለመወራረስ የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።

በማሠልጠኛ ማዕከሉ የተቀናጀ ሥልጠና ለመስጠት ምቹ መሰረተ ልማት እየተገነባ መኾኑን ማስረዳታቸውን ከሀገር መከላከያ ሚኒስቴር ማኅበራዊ ገጽ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበተዛባ መንገድ በተሰራጨ መረጃ ተገቢ ባልኾነ ግጭት ውስጥ መግባታቸውን የገለጹ 127 ዜጎች የተሀድሶ ሥልጠና ወስደው ወደ ማኅበረሰቡ ተቀላቀሉ።
Next article“በአማራ ክልል ከተሞች 44 ሺህ ቤቶች ይገነባሉ” የክልሉ ከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ