“ምልክቱ ይህ ነው የንጉሥ ሞት ሀዘን ጣይቱ ስትጨልም ጨረቃ ደም ስትኾን”

146

ባሕር ዳር: ታኅሳስ 3/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ንጉሥ ባለፈ ዘመን ሀዘን ይበዛል፤ ደስታ ይደበዝዛል፤ ሕዝብ ይሸበራል፤ ለቅሶ ይኖራል፤ ደረት መድቃት፣ ፊት መንጨት ይበረክታል፡፡ አምላክ የቀባው፣ ሕዝብ ይጠብቅ ዘንድ የመረጠው፣ በትረ መንግሥት ያስጨበጠው፣ ዘውድ የጫነው፣ መሪ፣ አሻጋሪ እንደኾነ ይታመናል እና ንጉሥ በሞተ ጊዜ ሀዘኑ ጥልቅ ነው፡፡

ደግ ንጉሥ ብርቱ እረኛ ነውና ሕዝቡን ይጠብቃል፤ ከጠላት መንጋጋ ይከላከላል፤ የመከራ ባሕርን ያሻግራል፤ በጨለመ ዘመን በብርሃን ይመራል፡፡ የሀገሬው ሰው ንጉሥን ከመንበሩ ጠብቅልን እያለ የሚማጸነውም ለዛ ነው፡፡ ንጉሥ በመንበሩ ሲኖር፣ ዙፋን ሲከበር ሀገር ይከበራል፤ ሕዝብም ይኮራልና፡፡

ደጋጎቹ አምላክ ቀብቶ የሰጣቸውን ንጉሳቸውን ይጠብቅላቸው ዘንድ ይማጸናሉ፤ በነጋ በጠባ ቁጥር በዙፋኑ በክብር ይኖር ዘንድ ለአምላካቸው ያሳስባሉ፤ ለንጉሡ ይታዘዙለታል፤ ለንጉሥም እድሜ ይለምኑለታል፤ እጅ ይነሱለታል፤ በቃሉ ይኖሩለታል፤ ግብር ይገብሩለታል፡፡

እሳቸው የከበረ ስም ያላቸው፤ ታሪክ ከፍ አድርጎ የመዘገባቸው፤ ሀገር የኮራችባቸው ኃያል ንጉሥ ናቸው እና የሀገሬው ሰው አብዝቶ ይወዳቸዋል፡፡ ይሳሳላቸዋል፤ በዙፋናቸው በክብር ያኖራቸው ዘንድ ይማጸንላቸዋል፡፡ በፈረሳቸው ተቀምጠው፣ በሰረገላም አጊጠው በአደባባይ በታዩ ጊዜ እጅ እየተነሳ “ሺህ ዓመት ይንገሡ” ይባልላቸዋል፡፡

ነጻነት የሚደፍረውን፣ ሀገር የሚደርበውን፣ ሕዝብ የሚያስገብረውን፣ ሃይማኖት የሚያጠፋውን፣ ታሪክ የሚያጎድፈውን ቅኝ ገዢ እንዳልነበር አድርገውታልና፡፡ እንኳን ሲዋጉ ያያቸው፣ እንኳን ሲዘምቱ የተመለከታቸው፣ እንኳን የጦር ልብስ ለብሰው በቁጣ ሲገሰግሱ ያስተዋሏቸው ሰዎች ይቅርና የተረማመዱባቸው ሜዳዎች፣ ጎራዴ የመዘዙባቸው ኮረብታዎች፣ ጠላትን ድል የመቱባቸው ተራራዎች የእሳቸውን ስም ያውቃሉ፤ የከበረ ታሪካቸውን ይመሰክራሉ፡፡

አባት ኾነው ሳለ እንደ እናት ይጠራሉ፤ አባባ መባል ሲገባቸው እምዬ ይሰኛሉ፡፡ ግርማዊነትዎ ዳግማዊ ምኒልክ፡፡ ከሰው ተለይቶ ኖሮ እንደ ሰው ማለፍ አይቀርምና እርሳቸውም አለፉ፡፡ እርሳቸውም አፈር ለበሱ፡፡ ዳሩ አፈር የማይለብስ፣ ሞቶ የማይበሰብስ የከበረ ታሪክ፤ የገዘፈ ስም አላቸውና ትውልድ ሁሉ ይጠራቸዋል፤ እምዬ እያለ ያወሳቸዋል፡፡

ብልህ አባት ሲኖር ብቻ ሳይኾን ካለፈ በኋላ ሀገሩ ምን እንደምትኾን ያሳስበዋል፡፡ እምዬ ምኒልክም የማለፋቸው ዘመን መድረሱን ውስጣቸው እየነገራቸው በመጣ ዘመን የሀገራቸው የወደፊት እጣ ፋንታ ያማረ እና የተዋበ የሚኾንበት መንገድ አስጨነቃቸው፡፡ ከሕመማቸው እና ከቀረበው ሞታቸው የበለጠ የሀገራቸው ጉዳይ አሳሰባቸው፡፡ ሰው ማለት የራስ ዘመን ብቻ ሳይኾን የልጅ ልጅ ዘመንም የሚያስጨንቀው ነውና፡፡  ተክለጻዲቅ መኩሪያ አጼ ምኒልክ እና የኢትዮጵያ አንድነት በተነሰኘው መጽሐፋቸው ሲጽፉ “ንጉሠ ነገሥቱ ሕመም እንደ ጸናባቸው እና እርጅና እንደ ተጫናቸው በተረዱት ጊዜ ሀሳባቸው እና ስጋታቸው ያስተካከልሁት የኢትዮጵያ አንድነት ይፈረስ ይኾን? በዙሪያዬ በኔ ሰበብ በንጉሠ ነገሥትነቴም ምክንያት ባንድ ሥልጣን የተሳሰሩት መሳፍንት እና መኳንንት እኔ ስሞት ተከፋፍለው በመዋጋት በኢትዮጵያ አንድነት ላይ አደጋ ይመጣ ይኾን?” የሚል ነበር ብለዋል፡፡

ይሄን ስጋት የጣለባቸው ከዘመነ መሳፍንት ጀምሮ የነበረው የእርስ በእርስ ጦርነት ነው፡፡ ንጉሥ አልፎ ንጉሥ ሊነሳ ነው በተባለ ጊዜ ጉልበታሙ ይበረክታል፡፡ አልገብርም፣ አላጎነብስም፣ ለዙፋን አልገዛም የሚለው ብዙ ነውና፡፡ ምኒልክ እርሳቸውን የሚተካ እና ዙፋናቸውን የሚወርሰውን እያመቻቹ ለመኳንንቱ እና ለመሳፍንቱ ብርቱ ቃል ሲያስተላልፉ “ኢትዮጵያ አንድ ኾና ከቶ ለጠላት ተሸንፋ አታውቅም፤ በታሪክም የለ” ብለው ነበር፡፡ የንጉሡን ቃል እውነትነት የኢትዮጵያ ታሪኮች ይመሰክራሉ፡፡ ኢትዮጵያዊያን አንድ ከኾኑ ጠላት አይደለም ሊያሸንፋቸው ሊደፍራቸው አይቻለውምና፡፡

ንጉሡ አልጋ ወራሻቸውን ባስተዋወቁበት ዘመን አንድነት እንዲጠና፣ መለያዬት እንዳይመጣ፣ ሀገር እንዳይጠፋ፣ ጠላት ደስ እንዳይለው፣ ሀገር  ተቆርሳ እንዳትሄድ፣ ሕዝብ በባርነት እንዳይገዛ፣ የተሠራው ሥርዓት እንዳይደፈርስ፣ የቀናው መልሶ እንዳይጠፋ ታላቅ የአደራ ቃል አስቀምጠዋል፡፡

ንጉሠ ነገሥት ምኒልክ ለሚወዱት እና ለሚወዳቸው ሕዝባቸው የአደራ ቃል ሲተዉ “ልጆቼ ወዳጆቼ አንዱ በአንዱ ምቀኝነት ይቅር፤ የአንዱን ሀገር አንዱ እደርበዋለሁ እንዳትባባሉ፡፡ እኔ እስካሁን በፍቅር እንዳኖርዃችሁ እናንተም ተስማምታችሁ በፍቅር እንድትኖሩ እለምናችኋለሁ፡፡ እናንተ አንድ ልብ ከኾናችሁ በምቀኝነት እርስ በእርሳችሁ ተዋግታችሁ ካላለቃችሁ በስተቀር ሀገራችንን ለሌላ ባዕድ አትሰጡትም፡፡ ክፉ ነገር ሀገራችንን አያገኘውም፡፡ ነፋስ እንዳይገባባችሁ፡፡ ሀገራችሁን በየአላችሁበት በርትታችሁ ጠብቁ፤ ወንድሜ ወንድሜ ተባባሉ፡፡ ሀገራችሁን ጠብቁ፤ አደራ ብያችኋለሁ፡፡ አደራ የሚባል ሰው የታመነ ነውና እኔም ሁላችሁንም አምናችኋለሁ፡፡ ከዚህም ከጻፍኩት ቃል የወጣ በሰማይም በምድርም የተረገመ ይሁን፡፡ እኔም ሳለሁ ከፈቃዴ የወጣ ልጅ ረግሜአለሁ” አሉ፡፡

እኒያ ትናንት ላይ ቆመው ነገ እና ከነገ ወዲያ ያለውን ዘመን የሚተነብዩ ብልህ ንጉሥ አንድነት ይጠበቅ፣ ሀገር ትጸና ዘንድ አደራ አሉ፡፡ ሕዝባቸውን ያምኑታል፤ ላመኑትም ሕዝብ አደራ ሰጡት፡፡ እርሳቸው እንዳሉ አደራ የሚሰጠው የታመነ ሰው ነው፡፡ ታዲያ በዚህ ዘመን ምን ያክል ለሀገር የታመነ ሰው ይኖር ይኾን?  ምን ያክልስ በምቀኝነት ያልተጠላለፈ ይኖር ይኾን?  ምን ያክልስ ከአንድነት ይልቅ መለያዬት የተጠናወተው ይኖር ይሆን? ምን ያክልስ ሀገር ከማግዘፍ ይልቅ ሀገር ማሳነስ የሚያስደስተው ይኖር ይኾን?

ከሰው ከፍ ብሎ ኖሮ እንደ ሰው መሞት፤ እንደ ሰው አፈር መልበስ፤ ክንድን መንተራስ አይቀርም እና ታላቁ ንጉሥ የእረፍታቸው ጊዜ ቀረበ፡፡ አጀብ የሚበዛላቸው፣ ኃያላኑ ሁሉ ዝናቸውን በሩቅ ሰምተው የተርበደበዱላቸው፣ ድል አድራጊነት የተቸራቸው፣ ብልሃት እና ጥበብ የታደላቸው ታላቁ ንጉሥ ለዓመታት ከተቀመጡበት ዙፋናቸው፣ ከተዋበው እና ካማረው ቤተ መንግሥታቸው ተለይተው፤ በትረ መንግሥታቸውን ጥለው፣ ዘወዳቸውን ትተው ላይመለሱ ያንቀላፉ ዘንድ ግድ ኾነ፡፡

በፊት በኋላቸው፣ በግራ በቀኛቸው እንደ አንበሳ የጀገኑ፣ እንደ ነብር የፈጠኑ ጀግኖች የሚያጅቧቸው፣ በወርቅ የተንቆጠቆጠ ሠረገላ የሚጫንላቸው፣ እምቢልታ እየተነፋ፣ ከበሮ እየተመታ፣ ነጋሪት እየተጎሰመ እጅ የሚነሳላቸው፣ መኳንንቱ እና መሳፍንቱ ለክብራቸው የሚንበረከኩላቸው፣ የእልፍኝ አስከልካዮች፣ የጦር አበጋዞች፣ ዓለም አጫዋቾች የሚሳሉላቸው፣ በቤተ መንግሥት ጠጅ የሚጥሉት፣ ጠላ የሚጠምቁት፣ እንጀራ የሚጋግሩት፣ ጮማ የሚቆርጡት፣ መብራት ይዘው የሚያበሉት ለደስታቸው የሚፋጠኑላቸው ጀግናው የመጨረሻ ዘመናቸው ደረሰ፡፡ እኒያ መሸነፍን አምርረው የሚጠሉት፣ በድል የሚረማመዱት ኀያል ንጉሥ በመጨረሻም ለሞት እጅ ይሰጡ ዘንድ ግድ አላቸው፡፡

መኳንንቱ፣ መሳፍንቱ፤ ካህናቱ፤ መነኮሳቱ፣ ዲያቆናቱ፣ የጦር አበጋዞች፣ የእልፍኝ አስከልካዮች ሁሉም ዓመት በዓል ሊያከብሩ ሽር ጉድ ላይ ነበሩ፡፡ ምሥጋናው ከፍ ብሏል፤ ውዳሴው ምድራዊ ሳይኾን ሰማያዊ መስሏል፡፡ የታኅሣሥ በዓታ ለማርያም ዓመታዊ ክብረ በዓል ነበርና ሁሉም በዓሉን በደስታ እያሰበ ነበር፡፡ በቤተ መንግሥት  ግን የሀዘን ድባብ ጥሎ ነበር፡፡ ለምን ቢሉ እምዬ ምኒልክ ደክመዋል፤ ላይመለሱ ሊያንቀላፉ ተቃርበዋልና፡፡ 

ተክለጻዲቅ መኩሪያ በታሪክ መጻሕፋቸው ስለእረፍታቸው ሲጽፉ “ገናናው ንጉሠ ነገሥት በ1900 ዓ.ም የጀመራቸው በሽታ እየጸና ሄዶ በመጨረሻ ሰውነታቸው ዝሎ አንደበታቸው ተዘግቶ እንደቆዬ በታኅሣሥ 3 ቀን 1906 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡ የሸዋ ንጉሥ፣ በኋላም የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት በነበሩበት ዘመን ሁሉ ክፉውን በክፉ ሳይኾን ክፉውን በደግነት እየመለሱ፣ ጥፋትን ሁሉ በትዕግሥት እያሸነፉ፣ ሀገር የሚሰፋበትን ልማት የሚዳብርበትን፣ ሕዝብ እረፍት እና ሰላም የሚያገኝበትን ከማሰብ እና ከመፈጸም አልተቆጠቡም፡፡ የአውሮፓን ኃያል መንግሥት በጦር ሜዳ በማሸነፍ ኢትዮጵያን በዓለም እንድትደነቅ አድርገዋል” ብለዋል፡፡

ጳውሎስ ኞኞ ደግሞ ብላታ መርስኤ ሀዘን ወልደቂርቆስን ጠቅሰው ሲጽፉ “አጼ ምኒልክ ሕመም ጸንቶባቸው ነበርና በታኅሣሥ 3 ቀን 1906 ዓ.ም በዕለተ አርብ ሞቱ፡፡ ወዲያው እንደሞቱ የግቢያቸው ሥራተኞች የልቅሶ ድምጽ አሰሙ፡፡ ነገር ግን የልጅ ኢያሱ ባለሟሎች ሀገር እንዳይሸበር ሰግተው በቶሎ ዝም አሰኟቸው”  በማለት ከትበዋል፡፡

የአጼ ምኒልክ ሞት በቶሎ ይፋ እንዳልኾነ ይነገራል፡፡ ይሄም የኾነው ታላቁ ንጉሥ መሞታቸው በተሰማ ጊዜ ሀገር እንዳይናጋ፣ ሥርዓት እንዳይደፈርስ፣ ሕዝብ እንዳይሸበር፣ ሀዘንም እንዳይበዛ ተፈልጎ ነበር፡፡ ንጉሡ የሉም በተባለ ጊዜ አልገብርም ብሎ የሚነሳ እንዳይኖር፤ ዙፋኑ መልሶ እስኪጸና፣ ወራሹም እስኪጠናከር መቆዬት ያስፈልግ ነበርና የንጉሡ ሞት ምስጢር ኾነ፡፡

“የአጼ ምኒልክን አስከሬን አሽከሮቻቸው እንደ ነገሥታት ማዕረግ አምሮ በተሠራ ብረት ሳጥን አድርገው በቤተ መንግሥቱ ግቢ ውስጥ ባለችው በስዕል ቤት ኪዳነምሕረት ቤተክርስቲያን በክብር አስቀመጡት፡፡ ባለቤታቸው እቴጌ ጣይቱ እና ልጃቸው ወይዘሮ ዘውዲቱ በሣጥኑ አጠገብ ኾነው መሪር ለቅሶ ያለቅሱ ነበር” ብለዋል ጳውሎስ እኞኞ በታሪክ መጻሕፋቸው፡፡
ታላቁ ንጉሥ እንደተራራ የገዘፈ ታሪክ ጥለው ባለፉ ጊዜ ንግሥት ኾነው ከአጠገባቸው የተቀመጡት፣ አብረው ጦር መርተው ድል ያደረጉት፣ በብልሃታቸው አንቱ የተባሉት ባለቤታቸው እቴጌ ጣይቱ በለቅሶው ጊዜ አንዲህ ብለው ተቀኙ አሉ፡፡

“ ነጋሪት ማስመታት፣ እምቢልታ ማስነፋት ነበረ ሥራችን
ሰው መኾን አይቀርም ደረሰ ተራችን” 
ሰው መኾን አይቀርም እርሳቸውም አለፉ፡፡ ተራቸው ደረሰና ዳግም ላይመለሱ አሸለቡ፡፡ እንደ ንጉሥ አብረው የነገሡት፣ እንደ ሚስት በአንድ ቃል ኪዳን የተሳሰሩት፣ እንደ መሪ ለሀገር እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ እንደ አንድ ልብ መካሪ ኾነው የኖሩት እቴጌ  ባለቤታቸው ሲያልፉ ያላዘኑ ማን ያዝናል፡፡ ልጃቸው ዘውዲቱም እያለቀሱ ለአባታቸው ተቀኙ፡፡
“ምልክቱ ይህ ነው የንጉሥ ሞት ሀዘን
ጣይቱ ስትጨልም ጨረቃ ደም ስትኾን” አሉ፡፡ ንጉሥ ሲሞት ብዙ ነገር ይቀየራል፡፡ ንጉሥ ሲያልፍ እልፍ ነገር ይናጋልና ልጃቸው የረቀቀ ቅኔ ተቀኙ፡፡ አልቅሰው አስለቀሱ፡፡ አዝነው አሳዘኑ፡፡ በዚህ ብቻ አላቆሙም የአባታቸውን ሀዘን የሚገልጹበት ሌላም ተቀኙ፡፡ 

“33 ዘመን የበላንበቱ የጠጣንበቱ
የታኅሣሥ በዓታ ለት ተፈታ ወይ ቤቱ” በማለት ስለአባታቸው እየተቀኙ አለቀሱ፡፡ አስለቀሱ፡፡  ባለቤታቸው፣ ልጃቸው፣ መኳንንቶቻቸው እና መሳፍንቶቻቸው ብቻ ሳይኾኑ የሚወዳቸው፣ የሚያከብራቸው እና የሚሳሳላቸው የሀገሬው ሰውም ንጉሡ ሲሞቱ  አለቀሰላቸው፡፡ አዘነላቸው፡፡ ተቀኙላቸውም፡፡
“ምኒልክ መጓዙን የምትጠይቁኝ
ፊትም አላለፈ ኋላም አይገኝ፡፡
አርባ ስድስት ዓመት የገዛኸው ንጉሥ
እንዳለህም ስጠኝ ከሌለህም ላልቅስ” በማለት አለቀሰላቸው፡፡ ስመ ገናናው ንጉሥ ከ110 ዓመታት በፊት ልክ በዛሬዋ ቀን ነበር ሕይወታቸው ያለፈው፡፡ ታላቅ ታሪክ የሠራ ይዘከራል፡፡ ሀገርን ከፍ ያደረገ በዘመናት መካከል ከፍ ይላልና ክፍ ብለው ይኖራሉ፤ ስማቸው እየተነሳ ይዘከራሉ፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከየምድቡ አላፊ ቡድኖች የሚለዩበት የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የምድብ የመጨረሻ ጨዋታዎች ምሽቱን ይከናወናሉ።
Next articleበተዛባ መንገድ በተሰራጨ መረጃ ተገቢ ባልኾነ ግጭት ውስጥ መግባታቸውን የገለጹ 127 ዜጎች የተሀድሶ ሥልጠና ወስደው ወደ ማኅበረሰቡ ተቀላቀሉ።